ቀጥታ፡

የሰላም ሚኒስቴር ከጠቅላይ ምክር ቤቱ ጋር በትብብር መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 16/2017(ኢዜአ)፦ የሰላም ሚኒስቴር ከእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጋር በትብብር መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።

የሰላም ሚኒስትሩ መሐመድ እድሪስ   ከምክር ቤቱ አመራሮችና የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ትውውቅና ውይይት አድርገዋል።

ጠቅላይ ምክር ቤቱ በቀጣይ በሚያካሄደው የመጅሊስ ምርጫ መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቋል።


 

በውይይቱ ላይ የሰላም ሚኒስትሩ መሐመድ እድሪስ  ለችግሮች መፍቻ የሚሆን ባህልና ልምድ ያላት ኢትዮጵያ ዜጎች በሰላም እጦት ምክንያት ለችግር መዳረግ የለባቸውም ብለዋል።

በዚህ ረገድ የኃይማኖት ተቋማት ሚና የላቀ በመሆኑን ለሰላም አበክረው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

በአፋርና በሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ የነበረውን አለመግባባትና ግጭት ለመፍታት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤቱ ለሰራው ገንቢ ሥራ ምስጋና አቅርበዋል።

በተመሳሳይ የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሼይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ የኢትዮጵያን ስም በዓለም መድረክ ከፍ ለማድረግ እየሰሩ ያለውን ሥራም ሚኒስተሩ አድንቀዋል።

ምክር ቤቱ ሁሉን አቀፍ የሰላምና የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ እንዲቀጥል ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የሰላም ሚኒስቴር ከሁሉም የእምነት አባቶችና ተቋማት ጋር በትብብር ይሰራል ያሉት ሚኒስትሩ መጭው የመጅሊስ ምርጫ በሰላማዊ ሁኔታ እንዲካሄድ መንግስት አስፈላጊውን እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ በበኩላቸው የሙስሊሙን አንድነትና አገራዊ ሰላምን ለማጠናከር ጠቅላይ ምክር ቤቱ የተለያዩ ሥራዎች እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም