ቀጥታ፡

የአንካራው ስምምነት የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስኬት የታየበት ነው

ሀዋሳ፤ ታህሳስ 16/ 2017 (ኢዜአ):- የአንካራው ስምምነት የኢትዮጵያ የመደራደር አቅምና የዲፕሎማሲ ስኬት ማሳያ  መሆኑን  አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የተለያዩ አካላት ገለጹ። 

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ብሔራዊ ጥቅምን ያስቀደመና የጎረቤት አገራትን የጋራ ተጠቃሚነት መርህን ያከበረ አካሄድን የሚከተል ነው። 

ይህም የመደራደር አቅምን በማሳደግ ስኬታማ ዲፕሎማሲን ለመተግበር አስችሏል ሲሉም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል። 

የታሪክ መምህርና ፖለቲከኛው በለጠ ስገቦ እንደገለጹት፤ የአንካራው ስምምነት የኢትዮጵያ ሰላም ተኮር የዲፕሎማሲ አካሄድ ስኬት ነው፤ አገሪቷ በስምምነቱ ያሳየችው ብስለትና የዲፕሎማሲ ከፍታ ለሌሎች አገራት ጭምር አስተማሪ ነው። 

የቀይ ባህርና ምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ቁልፍ ስትራቴጂክ ቦታ መሆኑን ያስታወሱት አቶ በለጠ፤ አካባቢው ያለውን ዕድል ለመጠቀም ሰላም ቀዳሚ በመሆኑ ስምምነቱ ወሳኝ እንደነበር አስረድተዋል።  

የባህር በር ማግኘት የአገሪቷን ኢኮኖሚ ለማሳደግ፣ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትንና ተመራጭነትን ለማላቅ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ "የአንካራው ስምምነት ይህን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማሳካት ያግዛል" ብለዋል። 

አገሪቱ አማራጭ የባህር በር ለማግኘት የጀመረችው በዕውቀት ላይ የተመሰረተ አካሄድ ግቡን እንዲመታ የውስጥ ሰላምንና አንድነቱን በማጠናከር መላው ዜጋ የሚጠበቅበትን ሊወጣ እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።


 

''የቀይ ባህር አካባቢ ወሳኝ ቀጣና በመሆኑ የዓለም አቀፍ ሀያላን አገራት ፍላጎት በግልጽ ይታይበታል'' ያሉት ደግሞ የዓለም አቀፍ ታሪክ፣ የቀይ ባህርና ቀጣናው ጉዳዮች ተመራማሪ አቶ ወሰንየለህ  ስምኦን ናቸው።  

በውስጥና ውጭ ተጽዕኖዎች አገሪቷ የባህር በር ማጣቷና ከዚህ ወሳኝ ቀጣና ዕድል ተቋዳሽ መሆን ያለመቻሏ የትውልድ ቁጭት ሆኖ መዝለቁን አመልክተዋል። 

መንግስት ለዚህ መፍትሄ ለማምጣት የወሰደው ቁርጠኝነትና እያደረገ ያለው ዓለም አቀፍ ሁኔታን የተረዳ የዲፕሎማሲ አካሄድ የሚደነቅ ነው ብለዋል። 

የአንካራው ስምምነት አገሪቷ የምትከተለው የዲፕሎማሲ አካሄድ ስኬታማነት እና የመደራደር አቅም ከፍታ ማሳያ መሆኑንም ጠቅሰዋል። 

የኢትዮጵያ መንግስት የሚከተለው አብሮ የመልማትና የሰላም አማራጭ ሁለቱንም ወገኖች አትራፊ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል። 

በዚህም ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ልቃ ታይታለች ያሉት አቶ ወሰንየለህ፤ የባህር በር ጥያቄዋ ዓለም አቀፋዊ አጀንዳ እንዲሆን አድርጋለች ይህ ደግሞ ሌላው የዲፕሎማሲ ስኬት ነው ብለዋል። 

የባህር በር ጥያቄ በተያዘው ሰላማዊና ሁሉንም በሚጠቅም መልኩ ተፈጻሚ እንዲሆን ከመንግስት ጎን በመሆን የሚጠበቅብንን ሁሉ ማድረግ ይገባናል ብለዋል። 

ኢትዮጵያና ሶማሊያ በአንካራ የደረሱት ስምምነት ከአውሮፓ ህብረት እስከ አፍሪካ ህብረት እንዲሁም ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት(ኢጋድ) እስከ የተለያዩ ዓለም ተቋማትና አገራት እውቅና የቸሩት ነው።

በተርክዬ ፕሬዚደንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን አቅራቢነት ታህሳስ 2/2017ዓ.ም በአንካራ የተካሄደው የኢትዮጵያና የሶማሊያ ውይይት ሁለቱንም አገራት በሚያግባባ ስምምነት በስኬት መጠናቀቁን በወቅቱ ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም