የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት- አቶ ገብረመስቀል ጫላ - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት- አቶ ገብረመስቀል ጫላ
አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 16 /2017(ኢዜአ)፦ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የነበረው ህዝባዊ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ገለጹ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዋንጫ ዛሬ ማለዳ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ የገባ ሲሆን ከዚሁ ጋር ተያይዞ በጌዴኦ ዞን የግድቡ ግንባታ ሀብት የማሰባሰብ ክልላዊ መድረክ በዲላ ከተማ እየተካሄደ ነው።
ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ገብረመስቀል ጫላ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ለባርነት እና ለቅኝ ግዛት የማትበገር ሀገር መሆኗን የሚያሳይ ትልቅ ፕሮጀክት ነው።
የሕዳሴ ግድብ ከአፍሪካ ኩራት ፕሮጀክት ከመሆኑም ባሻገር የዐይናችን ብሌንነው ብለዋል።
ለግድቡ ግንባታ ሲደረግ የነበረው የህዝብ ተሳትፎ መጠናከር እንደሚገባው ገልፀው፤ እንደ ክልል የተጀመሩ ሀብት ማሰባሰብ ስራዎችም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት፣ የሕዳሴ ግድብ የሀገራችን የሉዓላዊነት መገለጫ ነው ብለዋል።
በህዝቦቿ አንድነት እና የጋራ በመተባበር የተጀመረው የህዳሴ ግድብ ከዳር ለማድረስ የተጀመሩት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
በዞኑ በዚህ የህዳሴ ግድብ የሀብት የማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱ ተጠቁሟል ።
በውይይቱ ላይ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ፀሐይ ወራሳ፣የመንግስት አመራሮች እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎችና የከተማ ነዋሪዎች ተሳታፊ መሆናቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።