የተለያዩ የፌደራል ተቋማት የአማቂ ጋዞች ልቀት ልኬት ዙሪያ የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
የተለያዩ የፌደራል ተቋማት የአማቂ ጋዞች ልቀት ልኬት ዙሪያ የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 16 /2017 (ኢዜአ)፦የተለያዩ የፌደራል ተቋማት የአማቂ ጋዞች ልቀት ልኬት ላይ በቅንጅት ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የተፈራረሙት ተቋማት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን፣የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣የማዕድን ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር፣የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ደን ልማት ናቸው።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር ኢ/ር) የታዳሽ ኢነርጂ ልማት ለአማቂ ጋዝ ልቀት ቅነሳ ያለውን አስተዋጽኦ በማስላት ሪፖርት ለማጠናቀርና የካርበን ንግድ ላይ በስፋት ለመሳተፍ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ለሊሴ ነሜ (ኢ/ር) ፈጣን የከተሞች መስፋፋት እና የሰዎች የአኗኗር ዘይቤ መቀየር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ተጋላጭነትን መጨመሩን ገልጸዋል።
ይህንን በመከላከል ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ብሎም ኢትዮጵያ በ2030 የበካይ ጋዝ ልቀትን 68 ነጥብ 8 በመቶ ለመቀነስ የገባችውን ቃል እውን ለማድረግ በትብብር መስራት ወሳኝ ነው ማለታቸውን ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።