ፊሽካዬ ማስተናገጃዬ፤ ሞባይሌ ግብር መክፈያዬ ነው- ሕይወትን ማቅለል የሚወዱት እማማ ፊሽካ! - ኢዜአ አማርኛ
ፊሽካዬ ማስተናገጃዬ፤ ሞባይሌ ግብር መክፈያዬ ነው- ሕይወትን ማቅለል የሚወዱት እማማ ፊሽካ!

እኒህ እናት የዘመነ ኑሮ፤ ቀለል ያለ ኑባሬ ይወዳሉ። በርግጥ የተጸውዖ ስማችው ቤዛዊት ኃይለስላሴ ይሰኛል። ብዙሃኑ ከተሜው ግን በ'እማማ ፊሽካ'ነት ያውቃቸዋል። በአዲስ አባበ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ ጠበብ ያለችው ምግብ ቤት ባለቤት ናቸው- እማማ ፊሽካ።
ገበያቸው የደራ ነው። ገበያቸውን ያደራው፤ እርሳቸውን ያሳወቃቸው ደግሞ አንድም ፊሽካቸው ነው፤ አንድም የምግባቸው አቀራረብና ስያሜ ነው። የምግብ ዋጋቸውም ቢሆን ተመጣጣኝ ነው።
ወደ እማማ ፊሽካ ቤት ጎራ ያለ ደንበኛ ሁሉ ዕጁን በቅጡ መታጠብ ግድ ይለዋል። ሳይታጠብ ወደ ማዕድ የሚቀርብ ደንበኛ ካስተዋሉ እማማ ፊሽካ እንደ ትራፊክ ፊሽካቸውን ያስጮሃሉ። ይህ ልዩ ክዋኔያቸው ደግሞ ዝናቸውን አስናኝቷል። ቤታቸውን አሳውቋቸዋል። ደንበኞችም፤ ሚዲያውም ወደ ወደ ደጃቸው እንዲደርስ ዕድል ፈጥሮላቸዋል። በደንበኞቻቸው ዘንድም ከበሬታን አትርፎላቸዋል።
እማማ ፊሽካ ሰኔ 14 ቀንን አይረሱትም። ለእርሳቸው ልዩ ቀን ነው። ለምን ቢሉ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ወደ እማማ ፊሽካ ቤት ጎራ ብለው ማዕዳቸውን ተቋደሰው ነበርና- 'ዶክተር ዐቢይ' የተሰኘውን ምግብ።
እማማ ፊሽካ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በድንገት ወደ ምግብ ቤታቸው መከሰታቸውን አስመልክቶ "በሕይወቴ ደንግጬ የማላውቀውን አይነት ድንጋጤ ነው የተሰማኝ" ብለው ነበር በወቅቱ።
እናም የዕድሜ ባለጸጋዋ ወይዘሮ ቤዛዊት ከንጋት እስከ ምሽት ፊሽካቸውን እንደ ሜዳሊያ አንገታቸው ላይ አንጠልጥለው ምግብ ቤታቸውን ይቆጣጠራሉ። የእማማ ፊሽካ ታማኝነትና ከበሬታም ከቤታቸው የተሻገረ ነው።
ለሙያቸው ብቻ ሳይሆን ለግብራቸውም ታምነዋል። ግብራቸውን በወቅቱና በታማኝነት ይከፍላሉ። ግብር መክፈል የተሻለች ሀገር ለመገንባት የሚያግዝ 'የሀገር አደራ፣የውዴታ ግዴታ' እንደሆነ ያምናሉ።
ለዚህም ወደ ገቢዎች ቢሮ በጊዜ ያመራሉ። ዳሩ በግብር አከፋፈል ስርዓቱ ለእማማ ፊሽካ መሰል ግብር ከፋዮች ቀላልና ምቹ አልነበረም። ወደ ግብር መክፈያ ቦታዎች መመላለሱና ወረፋ መጠበቁ ከስራ ባህሪያቸው ጋር አብሮ አልሄድ እያላቸው ሲቸገሩ ቆይተዋል።
ዛሬ ግን ይህን እንግልት የሚቀርፍ ፈጣንና ምቹ የግብር አከፋፈል ስርዓት መዘርጋቱን ወይዘሮ ቤዛዊት ይናገራሉ። ድሮ 'ሲስተም የለም' እየተባሉ የሚጉላሉት አሰራር አሁን በቀላሉ ስራ ቦታቸው ሆነው ግብራችውን መክፈል እንዲችሉ አስችሏቸዋል። ቀለል ያለ የኑሮ ዘይቤ ለሚሹ ለእርሳቸው አይነት ሰዎች ይህ ወደር የሌለው ደስታ ፈጥሮላቸዋል።
የዲጂታል ግብር መክፈያ ቴክኖሎጂው ለዕድሜ ባለጸጋዋ እማማ ፊሽካ በፊሽካቸው ደንበኞቻቸውን እንዲያስተናግዱ፤ በሞባይላቸው ደግሞ ግብራቸውን እንዲከፍሉ አስቸሏቸዋል።
"ፊሽካዬ ማስተናገጃዬ፤ ሞባይሌ ደግሞ ግብር መክፈያዬ" የሚሉት እማማ ፊሽካ፤ ሕይወት ቀለል እንዳለላቸው ይግልጻሉ።
በርግጥ በቴክኖሎጂ የታገዘ የግብር አከፋፈል ስርዓት ለንግዱ ማህበረሰብ በጅቷል። እንደ እማማ ፊሽካ ሁሉ አቶ ደጉ ሃብቴ እና አቶ መላኩ መና፤ የዘመነ ግብር አከፋፈል ሕይወትን ቀለል እንዳደረገላችው ይናገራሉ።
የዲጂታል ቴክኖሎጂው ባሉበት ሆነው በቀላሉ መክፈል በማስቻሉ የጊዜ ብክነትንም፣ እንግልትንም ቀንሶላቸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሰውነት አየለ፤ በመዲናዋ ለሁሉም ግብር ከፋዮች የሚመች የዲጅታል አሰራር ስርዓት እንደተዘረጋ ይናገራሉ።
የዘመነ እና ቀልጣፋ ግብር አከፋፈል ስርዓቱን ለመተግበር የደረጃ " ሀ እና ለ " ግብር ከፋዮች "ኢ-ፐይመንት እና ኢ- ፋይናንስ" በተሰኙ ዲጂታል አማራጮች በቀላሉ ግብራቸውን እንዲከፍሉ ማስቻሉን ይገልጻሉ።
ይህ ደግሞ ደንበኞች ጊዜን፣ ገንዘብን እና ጉልበትን በቆጠበ መልኩ ያለምንም እንግልት ግብራቸውን እንዲከፍሉ እንደሚያግዝ ገልጸው፤ ደንበኞች ይህን አማራጭ በመቀጠም ግዴታቸውን ይወጡ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል።