ለገና እና ጥምቀት በዓላት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቱሪስቶችን በመቀበል በጥሩ መስተንግዶ የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ለገና እና ጥምቀት በዓላት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቱሪስቶችን በመቀበል በጥሩ መስተንግዶ የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 16/2017(ኢዜአ)፦ለገና እና ጥምቀት በዓላት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቱሪስቶችን በመቀበል በጥሩ መስተንግዶ የቆይታ ጊዜ ለማራዘም በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ቱር ኦፕሬተሮችና የቱሪስት አስጎብኚዎች ገለፁ።
በኢትዮጵያ የተገነቡ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ልማቶች የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ምቹ ሁኔታ የፈጠሩ መሆኑንም ነው የገለጹት።
በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ያሏት ኢትዮጵያ በበርካታ ታሪኮች፣ ቅርሶችና ባህሎች የታደለች ሀገር ናት።
እነዚህን ባህላዊ፣ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ቅርሶች ለመጎብኘት ከሀገር ውስጥም ሆነ ከተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚመጡ በርካታ ቱሪስቶች ይኖራሉ።
ኢትዮጵያ ካላት እምቅ የቱሪዝም ሃብት አኳያ ብዙም ሳይለማና በሚገባው ልክ ሳይተዋወቅ የቆየ ቢሆንም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ።
በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ የገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዲገነቡ በማድረግ የላቀ ሚና መወጣታቸውም ይታወቃል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን ከማስፋት ባለፈ ሀገሪቷ ያላትን እምቅ ሀብት የበለጠ እንዳታጎላና ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው።
የኢትዮጵያ ቱር ኦፕሬተሮች ማህበር ፕሬዚዳንት ፍጹም ገዛሃኝ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች በብዙ ቁጥር ኢትዮጵያን በተሻለ ለማስተዋወቅ ዕድል ይሰጠናል ብሏል።
የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ኤንዲ አሰፋ፤ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የቱሪዝም ሃብት በአግባቡ ለማስተዋወቅ ምቹ ዕድል መፈጠሩን ያነሳሉ።
በቀጣይ ለሚከበሩት ገና እና ጥምቀት በዓላት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቱሪስቶችን በመቀበል በጥሩ መስተንግዶ የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው፥ ለዚህም በተለያዩ ቦታዎች የተገነቡ የቱሪስት መዳረሻዎች ትልቅ ሚና አላቸው ብለዋል።
የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ከተማዋ ቀደም ሲል የነበራትን ስም የቀየረ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የቴማ ኢትዮጵያ አስጎብኚና ስራ አስኪያጅ ቴድሮስ ሰለሞን ናቸው።
ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ ከተማዋ ይመጡ የነበሩ እንግዶች ቆይታችውን የማራዘም ፍላጎታቸው መጨመሩን አንስተዋል።
በከተማዋ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ልማቶች የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ምቹ ዕድል መፍጠሩን የኢትዮጵያ ቱር ኦፕሬተሮች ማህበር ፕሬዝዳንት ፍጹም ገዛሃኝ ገልጸዋል።
የቱሪስት አስጎብኚዎቹ ክብሮም ተስፋዬና ኤንዲ አሰፋ፥ የቱሪስቶችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ አገልግሎት በመስጠት የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ዝግጅት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።
ለዚህ ደግሞ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየሰሩ መሆኑን በማንሳት።