ቀጥታ፡

በማያ ከተማ አስተዳደር ባለፉት አምስት ወራት ከተለያዩ ዘርፎች ከ866 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል

ማያ፤ታህሳስ 16/2017(ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል ማያ ከተማ አስተዳደር ባለፉት አምስት ወራት ከተለያዩ ዘርፎች ከ866 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የከተማ አስተዳደሩ ገቢዎች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በከተማ አስተዳደሩ የሚሰበሰበው ገቢ ለተለያዩ የልማት ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ እየዋለ መሆኑም ተገልጿል።

የማያ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብዲ ዩያ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በከተማ አስተዳደሩ ያሉትን የገቢ አማራጮችን አሟጦ በመጠቀም የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ በቅንጅት እየተሰራ ነው።

በተለይም ጽህፈት ቤቱ በበጀት ዓመቱ በሶስቱም ክፍለ ከተሞች የግብር ገቢ የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር የተሻለ ገቢ የመሰብሰብ ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል።

ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የሚታዩ ውስንነቶችን በመፍታት ለግብር ከፋዩ ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸውም ተናግረዋል።

በዚህም በከተማ አስተዳደሩ ባለፉት አምስት ወራት በሁሉም ዘርፎች 866 ሚሊዮን 852 ሺህ 272 ብር ገቢ መሰብሰቡን የተናገሩት አቶ አብዲ፤ ይህም የእቅዱን መቶ በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።

ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም ገቢው በእጥፍ ብልጫ እንዳለው በማመልከት።

ለስኬቱም ግብር ከፋዩን ያሳተፈ የገቢ አሰባሰብ ስራ ማከናወን በመቻሉና ህገ ወጥ ነጋዴዎችን ወደ ህጋዊነት ለማስገባት በተሰሩ ስራዎች መሆኑን ጠቁመዋል።

በከተማ አስተዳደሩ የሚሰበሰበው ገቢ ለተለያዩ የልማት ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ እየዋለ መሆኑን ጠቁመው፤ ከእነዚህም መካከል ለኮሪደር ልማት፣ለአስፋልትና ጌጠኛ መንገድ ዳር ግንባታ እንዲሁም የኤሌክትሪክ እና ለተለያዩ የቢሮ ህንፃ ግንባታና ለሌሎች የልማት ፕሮጀክት ስራ እየዋለ መሆኑን አቶ አብዲ ጠቅሰዋል።

በማያ ከተማ አስተዳደር በተያዘው በጀት ዓመት ከአንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አቶ አብዲ አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም