ቀጥታ፡

የቁልቢ ገብርኤል ንግስ በዓል በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል -የፀጥታ ምክር ቤቱ

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 16 /2017 (ኢዜአ)፦በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበረው ቅዱስ ገብርኤል የንግስ በዓል በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው የፀጥታ ዝግጅት መደረጉን የድሬዳዋ አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

የፀጥታ ምክር ቤቱ የበዓሉ ን አከባበር አስመልከቶ በተዘጋጀው ዕቅድ ዙሪያ ውይይት አካሂዷል::


 

መድረኩን የመሩት የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር አለሙ መግራ በዓመት 2 ጊዜ የሚከበረውን የቁልቢ ገብርኤል ንግስ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግርና ያለ አንዳች የትራፊክ አደጋ እንዲከበር የምሥራቅ ኢትዮጵያ የፀጥታ ግብረ ኃይል ዓመታዊ የዕቅድ አካል በማድረግ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልፀዋል።

በዓሉ በፍፁም ሰላማዊነት እንዲከበር የህብረተሰቡን ስጋቶች በመለየት የፀጥታ ምክር ቤቱ በተቀናጀ መልኩ ወደ ስራ መግባቱን አስረድተዋል፡፡

ኮሚሽነሩ አክለውም ፤ የድሬዳዋ አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት አባል ከሆኑት የሀገር መከላከያ ሠራዊት የምሥራቅ ዕዝ፣የፌዴራል ፖሊስ ምስራቅ ፈጥኖ ደራሽ ፣የድሬዳዋ አስተዳደር ፍትህ ፀጥታና ህግ ጉዳዮች ቢሮ ፣የድሬዳዋ ፖሊስ ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ድርጅትን በማካተት ለበዓሉ አስፈላጊው የዝግጅት ተደርጓል ሲሉ ጠቁመዋል።

ለበዓሉ ወደ ድሬዳዋና ቁልቢ የሚመጡ ምዕመናን ያለምንም ሃሣብ ወደ ስፍራው በመምጣት እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ኮሚሽነር አለሙ መግራ ለመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞችም የእንኳን አደረሳች መልዕክት ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ከድሬዳዋ አስተዳደር ጸጥታ ምክር ቤት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም