ኮርፖሬሽኑ ከሀገራዊ ሪፎርሙ የተቀዳ የለውጥ እሳቤ እና ተቋማዊ ማሻሻያ ማድረጉ ውጤታማ አድርጎታል - አቶ ረሻድ ከማል - ኢዜአ አማርኛ
ኮርፖሬሽኑ ከሀገራዊ ሪፎርሙ የተቀዳ የለውጥ እሳቤ እና ተቋማዊ ማሻሻያ ማድረጉ ውጤታማ አድርጎታል - አቶ ረሻድ ከማል
አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 15/2017(ኢዜአ)፦ የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከሀገራዊ ሪፎርሙ የተቀዳ የለውጥ እሳቤ እና ተቋማዊ ማሻሻያ ማድረጉ ውጤታማ እንዳደረገው የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል ገለጹ።
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የተቋማዊ ሪፎርም ልምዱን ለኢትዮጵያ የማዕድን ኮርፖሬሽን አጋርቷል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ሪፎርም ማዕከል በአመራሩና በሰራተኛው መካከል ወጥ የተግባርና የአመለካከት አንድነት በቅድሚያ ማረጋገጥ እንደነበር አውስተዋል።
ተቋሙ የለውጥ እሳቤ እና ተቋማዊ ሪፎርም አጀንዳም ከሀገራዊ ሪፎርሙ የተቀዳ መሆኑን አመልክተዋል።
በአመራሩና በሰራተኛው መካከል የተግባርና የአመለካከት አንድነት ለማምጣት የተቀረጸው የሪፎርም አጀንዳ መሳካት ለሌሎች አንኳር የሪፎርም አጀንዳዎች መሳካት አስተዋጽኦ ማድረጉንም ተናግረዋል።
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን መለወጥ እና ስኬታማ ሞዴል ተቋም መሆን መቻሉ በተመሳሳይ ችግር ያሉ ተቋማት ለመለወጥ ለሚያደርጉት ጥረት ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል አቶ ረሻድ።
የኢትዮጵያ ማዕድን ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቴዎድሮስ ጌታቸው የኮርፖሬሽኑ የሪፎርም ሂደትና የደረሰበት የስኬት ደረጃ ተቋሙ ተግባራዊ ለሚያደርገው ተቋማዊ ሪፎርም ትክክለኛ ሞዴል የሚሆን ነው ብለዋል።
የተቋሙ አመራሮች ከፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አመራሮችና ሰራተኞች ጋር ባካሄዱት ምክክርና ውይይት በተቋማቸው ተግባራዊ ለማድርግ ላቀዱት ሪፎርም በቂ ተሞክሮና ልምድ እንዳገኙ መግለጻቸውን ከፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።