የኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር ትራንስፖርት እንቅስቃሴ የፀጥታ ሁኔታ ማጠናከር የሚያስችል ውይይት ተደረገ

አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 15/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር ትራንስፖርት እንቅስቃሴ የፀጥታ ሁኔታ ማጠናከር የሚያስችል የባለድርሻ አካላት ውይይት ተደረገ።


 

ውይይቱ በገቢና በወጪ ምርቶች በማጓጓዝ ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ባለው የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር መሥመር ላይ አልፎ አልፎ በመሠረተ ልማት ላይ ከሚፈፀም ወንጀል ነፃ ለማድረግና ከሌሎች የወንጀል ስጋቶች ለማፅዳት ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።

በውይይቱ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ከኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር እና ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን በፀጥታው ዙሪያ ያሉ ችግሮችን በጥናት ለመለየት አቅጣጫ አስቀምጠዋል።


 

ባለድርሻ አካላቱ በቀጣይም የክልል የፀጥታና የክልል መስተዳድር አካላትን በጉዳዩ ላይ በማወያየት የአካባቢው ኅብረተሰብ ግንዛቤ በማሳደግ ውስን የፀጥታ ችግሮችን ለመቅረፍ በቁርጠኝነት እና በተነሳሽነት ለመስራት መስማማታቸውን ከፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም