በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የዕለት ደራሽ ሰብዓዊ ድጋፍ እየቀረበ ነው- የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የዕለት ደራሽ ሰብዓዊ ድጋፍ እየቀረበ ነው- የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን
ባሕር ዳር፤ ታህሳስ 15/2017 (ኢዜአ) ፡- በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ በምግብ እጥረት ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ እየቀረበ መሆኑን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን አስታወቀ።
በአካባቢው የነበረው የፀጥታ ችግር ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ ለማድረግ መስተጓጎል ፈጥሮ እንደነበር ገልጿል።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ሰርክአዲስ አታሌ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ የእርዳታ እህሉ እየቀረበ ያለው በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ ለምግብ እጥረት ለተጋለጡ 110 ሺህ ወገኖች ነው።
በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ለምግብ ችግር ለተጋለጡት ወገኖች የምግብ እህል እየቀረበ ያለው በመንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ርብርብ መሆኑንም ገልጸዋል።
በአካባቢው በነበረው የሰላም እጦት ምክንያት የዝግጅት ሥራዎች ተስተጓጎለው እንደነበረ አብራርተዋል።
በተለይ እርዳታው ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች እንዲደርስ የአካባቢው ማህበረሰብ ሚናውን በመወጣት እያደረገ ላለው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም በምግብ፣ በጤናና በውሃ በኩል ያለውን ችግር በጥልቀት ለይቶ ድጋፍ ለማቅረብ የተቀናጀና የተጠናከረ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።