የሀዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ንግሥ ክብረ በዓል ዝግጅት ተደርጓል- የከተማው ፖሊስ - ኢዜአ አማርኛ
የሀዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ንግሥ ክብረ በዓል ዝግጅት ተደርጓል- የከተማው ፖሊስ
ሀዋሳ ፤ ታኅሣሥ 15/2017 (ኢዜአ)፦ በሀዋሳ ከተማ ለቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ የንግሥ ክብረ በዓል አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ ሀላፊ ኮማንደር መልካሙ አየለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በየዓመቱ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በርካታ ምዕመናን ክብረ በዓሉን እንደሚታደሙ አስታውሰዋል።
በዓሉ ያለ ጸጥታ ስጋት በድምቀት ተከብሮ እስኪጠናቀቅ የጸጥታ ሀይሉ ከከተማው ማህበረሰብ ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል።
ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ የመከላከል እና በስርቆትና መሰል ወንጀሎች ተጠርጣሪዎችን በአስቸኳይ ፍርድ ለመስጠት ሁለት ጊዜያዊ ችሎቶች እንዲቋቋሙ መደረጉንም ጠቁመዋል።
የነዳጅ እጥረት እንዳያጋጥም ለእንግዶች ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ነዳጅ ማደያ መዘጋጀቱን እና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ከሆቴሎችና ከንግዱ ማህበረሰብ አባላት ጋር ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።
የከተማዋ ማህበረሰብ እንግዶችን ተቀብሎ የማስተናገድ ልምዱን እንዲተገብር እና ወንጀልን በጋራ በመከላከል ትብብሩን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
የሃዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ንግሥ ታኅሣሥ 19 ቀን 2017 ይከበራል።