በውጭ ካለው የሥራ ገበያ ፍላጎት ጋር የሚጣጣም የሰው ኃይል ለማቅረብ እየሰራን ነው- የኦሮሚያና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች - ኢዜአ አማርኛ
በውጭ ካለው የሥራ ገበያ ፍላጎት ጋር የሚጣጣም የሰው ኃይል ለማቅረብ እየሰራን ነው- የኦሮሚያና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 15/2017(ኢዜአ)፦ በውጭ ሀገር ካለው የሥራ ገበያ ፍላጎት ጋር የሚጣጣም የሰው ኃይል ለማቅረብ እየሰሩ መሆናቸውን የኦሮሚያና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ገለጹ።
ለሥራ ወደ ውጭ ሀገር የሚሰማሩ ዜጎች በቂ ዕውቀትና ክህሎት ጨብጠው እንዲሰማሩ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል።
ከውጭ ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት በማድረግ ዜጎች መብታቸው፣ ክብራቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ ለማስቻል ሀገራዊ ጥረቶችም ገቢራዊ እየተደረጉ ነው።
የውጭ ሀገር ገበያ በማፈላለግ፣ መዳረሻ ሀገራትን በመለየት ዜጎች ህጋዊ የስራ ዕድል እንዲያገኙ የተጀመሩ ሥራዎችም አወንታዊ ውጤቶች እየተገኙበት ነው፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየውም እስካሁን ከስድስት ሀገራትና ከተለያዩ ተቋማት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት በመፈፀም ዜጎች ወደ ውጭ ሀገር ሄደው እንዲሰሩ እየተደረገ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም ከውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ከክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊዎች ጋር ቆይታ አድርጓል።
የኦሮሚያ ክልል ሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ካሳ በበኩላቸው በክልሉ ለሥራ ወደ ውጭ የሚሰማሩ ዜጎችን አሰልጥኖ መላክ ላይ አበረታች ውጤቶች እየተገኙ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንዲያም ሆኖ ስልጠና በሚሰጡ አንዳንድ ኮሌጆች ላይ በአግባቡ ሥልጠና አለመስጠት ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመው የማስተካከያ እርምጃዎች መወሰዳቸውንም ገልጸዋል።
እንደ አቶ ሀብታሙ ገለጻ በክልሉ ከውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ጋር በተያያዘ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በተወሰዱ እርምጃዎች ውጤቶች ተገኝተዋል።
ስልጠናዎች በአግባቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ ከስልጠና ጥራት ጋር የተያያዙ ችግሮች እየተፈቱ መሆኑንም አስረድተዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ እንደገለጹት ከክልሉ ወደ ውጭ ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎች አስፈላጊውን ክህሎት ጨብጠው እንዲሄዱ ስልጠናዎች እየተሰጡ ነው።
በበጀት ዓመቱ 5 ወራት በመንግሥትና በግል ኮሌጆች ለ44 ሺህ ዜጎች ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።
ከዚህ ውስጥም ባለፉት አምስት ወራት ከ19 ሺህ 100 በላይ ዜጎች ወደ ውጭ ሀገር መሰማራታቸውን ተናግረዋል።
ለሥራ ፈላጊዎቹ በአንድ ማዕከል እንዲመዘገቡ በማድረግ፣ ተገቢው ሥልጠና መሰጠቱ እና የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምዘና እንዲወስዱ መደረጉን ጠቁመዋል።
የውጭ ሀገር የገበያ ፍላጎቱ አሁንም ከፍተኛ ነው ያሉት አቶ ሙስጠፋ ከፍላጎቱ ጋር የሚጣጣም የሰው ኃይል ለማቅረብ እንደ ክልል ሁሉን አቀፍ ጥረቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል።
አሁንም ከሕጋዊ መንገድ ይልቅ በሕገ ወጥ መንገድ ለመሄድ የሚፈልጉ ዜጎች መኖራቸው እንዲሁም የሕገ ወጥ ደላሎች ጉዳይ ዘላቂ መፍትሄ የሚፈልግ በመሆኑ እየሰራንበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያም የግንዛቤ ሥራዎችን በማካሄድ የዜጎችን ንቃተ ህሊና የማሳደግ ሥራዎች በትኩረት እንደሚከናወኑም አስረድተዋል።
በ2017 በጀት ዓመት አምስት ወራት ከ160 ሺህ በላይ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ወደተለያዩ የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት ማድረጋቸውን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በቅርቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።