ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ችግሮች በውይይትና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ሚናውን እንደሚወጣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ

ባህር ዳር፤ ታኅሳስ 15/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ችግሮች በውይይትና በሠላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ሚናውን እንደሚወጣ በክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታውቋል።

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዛሬ በባህር ዳር ከተማ የውይይት መድረክ አካሄዷል።


 

ምክር ቤቱ በወቅታዊ የሠላም ጉዳይና በአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ተግባር ዙሪያ መክሯል።

የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ተስፋሁን አለምነህ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በክልሉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በውይይትና በሠላማዊ መንገድ እንዲፈቱ መግባባት ላይ ተደርሷል።

በዚህ ረገድ የጋራ ምክር ቤቱ አባላት ለስኬቱ የሚጠበቅባቸው ሚና ለመወጣት መስማማታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የሚያደርጋቸው ጥረቶችን በመደገፍ ለስኬቱ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግም ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አባል ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ችግሮችን ከኃይል አማራጭ መለስ ባሉ ሰላማዊ መንገዶች እንዲፈቱ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።

በመድረኩ ኢዜማ፣ አብን፣ ብልጽግና፣ አዴሃን፣ የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ኢህአፓ፣ መኢአድ፣ የአማራ ግዮናዊ ንቅናቄ እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም