ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የጋራ ልማት፣ ሰላምና ብልጽግና ዕውን ለማድረግ የትብብር ጥረታችን ይቀጥላል- የሶማሊያ የውጭና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አሊ ኦማር

አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 15/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የጋራ ልማት፣ ሰላምና ብልጽግና ዕውን ለማድረግ የትብብር ጥረታችን ይቀጥላል ሲሉ የሶማሊያ የውጭና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አሊ ኦማር ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ የአንካራውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ለመተግበር ቁርጠኛ መሆኗንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገልጸዋል።

የአንካራውን ስምምነት በማፅናት በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ በሶማሊያ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ የተመራ ልዑክ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት እያደረገ ይገኛል።

የሶማሊያ የልዑካን ቡድን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ጋር ውይይት አድርጓል።

የሶማሊያ የውጭና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አሊ ኦማር፤ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገናል ሲሉ ተናግረዋል።

ከአንካራው ስምምነት በኋላ የመጀመሪያ ጉብኝታቸው መሆኑን ገልጸው፣ ስምምነቱን ገቢራዊ ለማድረግ የሚያስችል ውይይት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ዲፕሎሚሲያዊ እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን አንስተው የሁለቱን አገራት የጋራ ልማት፣ ሰላምና ብልጽግና ዕውን ለማድረግ የትብብር ጥረታችን ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያና ሶማሊያ ህዝቦች መካከል ያለውን ጠንካራ ወዳጅነት ለማስቀጠል ሶማሊያ ቁርጠኛ አቋም እንዳላት አንስተዋል።


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በበኩላቸው፤ የአንካራውን ስምምነት ገቢራዊ በማድረግ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር ቀጣይነት ያለው ውይይት እናደርጋለን ብለዋል።

የሶማሊያ ሰላም የኢትዮጵያ ሰላም መሆኑን ገልጸው፤ ሽብርተኝነትን በመከላከል በቀጣናው ሰላም ለማስፈን ትብብራችን ተጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት።

የውይይቱ ሂደት በጥሩ መግባባትና መተሳሰብ ላይ የተመሰረተ መሆኑን አንስተው ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርና ጠንካራ ትብብር ለመፍጠር እየሰራች መሆኑን አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት እልባት ለመስጠት በአንካራ ታኅሣሥ 2 ቀን 2017 ዓ.ም በአንካራ ስምምነት የተደረገ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ሞሐመድ ፍሬያማ ንግግር ማድረጋቸውም ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም