የደረቅ ወደብና ተርሚናሉ ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት ያከናወናቸው ተግባራት አበረታች ናቸው- ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
የደረቅ ወደብና ተርሚናሉ ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት ያከናወናቸው ተግባራት አበረታች ናቸው- ቋሚ ኮሚቴው
ድሬዳዋ፤ ታኅሣሥ 15/2017(ኢዜአ)፦ የድሬዳዋ ደረቅ ወደብና ተርሚናል የክዋኔ ኦዲት ግኝቶች በማስተካከል ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት ያከናወናቸው ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
የቋሚ ኮሚቴው አመራርና አባላት የድሬዳዋ ደረቅ ወደብና ተርሚናል እና የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠናን የስራ እንቅስቃሴዎች ተመልክልቷል።
የመስክ የስራ ጉብኝቱ ዓላማም የክዋኔ ኦዲት የባለፈው ዓመት ሪፖርትና በድሬዳዋ ደረቅ ወደብና ተርሚናል የስራ እንቅስቃሴዎች ላይ ያስቀመጠውን የስራ አቅጣጫና ግብረ መልስ መገምገም መሆኑም ታውቋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ የሺመቤት ደምሴ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የድሬዳዋ ደረቅ ወደብና ተርሚናል የተሰጣቸውን የአሠራር ክፍተቶችና የክዋኔ ኦዲት ግኝቶችን ለማስተካከልና ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት ያከናወናቸው ተግባራት አበረታች ናቸው።
ወደቡን ከድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና እና ከዘመናዊ የባቡር ትራንስፖርት ጋር በመሠረተ ልማቶች አሰናስሎ የወጭና ገቢ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ቀልጣፋ ለማድረግ የተሰሩ ሥራዎችን ተመልክተናል ብለዋል።
የክዋኔ ኦዲት ሪፖርቱ በአንድ ጊዜ የሚስተካከል ሳይሆን በሂደት የሚፈታ መሆኑን ጠቁመው፤ የተጀመሩት የማስተካከያ ስራዎች ግን አበረታች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በድሬዳዋ ደረቅ ወደብና ተርሚናል እንዲሁም በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና የተመለከቱት ዘመናዊ የተቋማት ግንባታም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባል ወይዘሮ አያንቱ ጉተታ በበኩላቸው በተቋማት የተመለከቱት የሪፎርም ትግበራና የለውጥ ሂደት የአገርን ከፍታና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ተቋማቱ የአካባቢውን ህብረተሰብ ማህበራዊ ችግሮች በማቃለልና ተጠቃሚነት እያረጋገጡ በመሆናቸውም ማህበረሰቡ ለተቋማቱ ጥበቃ የማድረግ ኃላፊነቱን በመወጣት ባለቤትነቱን ይበልጥ ማፅናት እንዳለበት አሳስበዋል።
የድሬዳዋ ደረቅ ወደብ እና ተርሚናል በቴክኖሎጂ የታገዙ አሠራሮች መዘርጋቱን የገለፁት ደግሞ በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ የወደብና ተርሚናል ዘርፍ ተወካይ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ብሩክ በዛ ናቸው።
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን በማድረግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን እያሳደገ ይገኛልም ብለዋል።