ቀጥታ፡

የአንካራው ስምምነት በቀጣናው ሽብርተኝነትን በመመከት በጋራ የመልማት ፍላጎትን ለማሳካት ያግዛል - የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር

ጅግጅጋ፣ ታህሳስ 15/2017 (ኢዜአ)፦ የአንካራው ስምምነት በቀጣናው የሽብር ቡድኖችን በመመከት የህዝቦችን በጋራ የመልማት ፍላጎት ዕውን ለማድረግ እንደሚያስችል ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር ገለጹ።

በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ሙስጠፌ በርከድ፤የኢትዮ-ሶማሊያ የአንካራ ስምምነት በሁለቱ መሪዎች የተፈጠረው አለመግባባት በንግግር ለመፍታት ያላቸውን አቅምና ቁርጠኝነት ያሳየ ነው።

ስምምነቱ ከሁለቱ አገራት ትብብር ባሻገር ለቀጣናው ሰላም ትልቅ ዕድል ይዞ እንደሚመጣ ገልጸዋል።

በቀጣናው የሽብር ቡድኖችን ጥቃትና የመስፋፋት ፍላጎት በማስቀረት ለህዝቦች የጋራ የመልማት ፍላጎትን ዕውን ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።

ሁለቱ አገራት በአንካራ የደረሱት ስምምነት በተለይም "የጋራ ጠላታቸው የሆነውን የአልሸባብ የሽብር ቡድን እንቅስቃሴን ለመግታት አዲስ የትብብር መንፈስ ይፈጥራል" ነው ያሉት።

የስምምነት ሂደቱን ተከትሎ በቀጣይ የሚኖረው ድርድር በመግባባትና በመልካም ጉርብትና ላይ በተመሰረተ አኳኋን መካሄድ እንደሚገባው ገልጸዋል።

በስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ ደህንነቱ የተጠበቀና ዓለም አቀፍ ዋስትና ያለው የወደብ አገልግሎት ፍላጎቷን ማሳካት የሚቻልበት ሁኔታ መኖሩንና የሶማሊያ መንግስት ደግሞ "የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለሰላምና መረጋጋት የከፈለውን የህይወት ዋጋ እውቅና መስጠቱ ብሔራዊ ጥቅምን ያማከለ ስኬታማ ስምምነት ነው" ብለዋል።

"በሁለቱ አገራት መሪዎች ውይይት እና በስምምነቱ ወቅት የኢትዮጵያ ፅኑ ፍላጎት የነበረው ሰላማዊ በሆነ መንገድ የባሕር በር የማግኘት ዓላማ እየተሳካ መምጣቱን ስምምነቱ አመላካች ይሆናል" ብለዋል

ይህ ስምምነት መሰረተ ልማትን በማስፋፋት ወጪና ገቢ ምርትን በማሳለጥ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት(ኢጋድ) በትብብር የማደግ መርህን መሰረት አድርጎ የተከናወነ መሆኑንም ምሁሩ ገልጸዋል።

ስምምነቱ የውጪ ጣልቃ ገብነትን በማስቀረት ሁለቱ አገራት ባላቸው የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብቶቻቸውን ለህዝቦች ዕድገትና ኑሮ መሻሻል እንዲያውሉ በር ከፋች መሆኑን በማውሳት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም