ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ሲካሄድ የቆየው የምክክርና አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ የተሳካ ነው - ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

አዳማ፤ ታህሣሥ 15/2017(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ሲካሄድ የቆየው የምክክርና አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ የተሳካ እንደነበር የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለጹ።

በተለይም በቅርቡ ከክልሉ መንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት የፈፀሙ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ተወካዮች በክልሉ በነበረው የምክክርና አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት መሳተፋቸው ትልቅ ስኬት መሆኑን ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ አስታውቀዋል።

በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ከታህሳስ 7/2017 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የአገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብ መርሃ ግብር የተሰበሰበውን አጀንዳ በማስረክብ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በርክክቡ ወቅት እንደገለፁት፤ የምክክርና አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ የተሳካ ነው ብለዋል።

በሂደቱ ከ7 ሺህ በላይ የህዝብ ተወካዮች በ640 የምክክር ቡድኖች በመደራጀት ሃሳብና አጀንዳቸውን በነፃነት ሲያነሱ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች፣ የተፅዕኖ ፈጣሪዎችና የሃሳብ መሪዎች ተወካዮች፣ የማህበራትና ተቋማት ተወካዮች ተሳፈዋል ብለዋል።

የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ያለገደብ ሃሳባቸውንና አጀንዳቸውን አሳታፊና አካታች በሆነ መንገድ አቅርበዋል ሲሉም ገልጸዋል።

ክልሉን ወክለው በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ ወኪሎች ምርጫ ከሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች ወኪሎች ምርጫ በነጻነት መከናወኑንም አንስተዋል።

በተለይም በቅርቡ ከክልሉ መንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት የፈፀሙ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ተወካዮች በክልሉ በነበረው የምክክርና አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት መሳተፋቸው ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።

በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲሳተፉ የተመረጡ የተለያዩ ማህበረሰብ ወኪሎች የተሰጣቸውን አደራ መወጣት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም