ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል አለበት - ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 15/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት አማራጭን ለማስፋት እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው፤ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ በሁዋጂያን እና በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ያደረገውን የመስክ ምልከታ አጠናቅቆ ግብረ-መልስ ሰጥቷል፡፡

የመስክ ምልከታ ቡድኑ አስተባባሪ ሙሉ ይራጋ ኮሚሽኑ የቅድመ ኢንቨስትመንት፤ የቢዝነስ ፕሮቶኮል፣ የፍቃድና ምዝገባ፣ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ፣ የድጋፍና ክትትል አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ ለማድረግ እየሰራቸው ያሉት ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የፈቃድ የምዝገባ፣ እድሳት፣ የባንክና ሌሎችም ስራዎች ባለሃብቱ ሳይጉላላ በአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲያገኝ መደረጉን በጥንካሬ አንስተዋል፡፡


 

ከማበረታቻ አገልግሎት ጋር በተያያዘ በኢንቨስተሮች ላይ ሲደርስ የነበረውን መዘግየት ለመቀነስ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት መሰራቱ የሚበረታታና እመርታዊ ለውጥ የታየበት አሰራር መሆኑን ነው አስተባባሪዋ የገለጹት።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ለባለሃብቱ የሚሰጡ የማበረታቻ አገልግሎቶች ለታለመላቸው ዓላማ ስለመዋላቸው ኮሚሽኑ እያደረገ ያለውን ድጋፍ ማጠናከር እንደሚገባው አመልክተዋል።

ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗን ተከትሎ ባለሃብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን በሀገሪቱ እንዲያፈሱና ዜጎች የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየከናወነ ያለውን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ተቋሙ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን ለመደገፍ እና አምራች ኩባንያዎች የሀገር ውስጥ ጥሬ እቃን እንዲጠቀሙ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ባለሀብቶች ከውጭ ምንዛሬ ጋር የሚያጋጥማቸው ችግር እንዲፈታ አማራጮችን የመፍጠር ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ለአሰራር እንቅፋት የሆኑ ችግሮች እንዲቀረፉ ድጋፍ እንዲያደርግ ኮሚሽነሩ መጠየቃቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም