ጥራቱን የጠበቀ የቡና ምርት ለዓለም ገበያ በማቅረብ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው - ባለስልጣኑ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 15/2017(ኢዜአ)፡- ጥራቱንና የምርት ዱካውን የጠበቀ ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

ቡና በዓለም ላይ በከፍተኛ መጠን ለግብይት ከሚቀርቡ ምርቶች መካከል አንዱ ሲሆን የተለያየ ጣእም ያለው ቡና ተወዳጅነቱና ተፈላጊነቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ ተፈላጊ ጣዕም ያለውን ቡና ማምረት የሚያስችል ተስማሚ የአየር ንብረት እንዳላት ይታወቃል፡፡

የቡና ምርት ጥራት ከማሳ እንክብካቤ ለገበያ እስከሚቀርብበት ድረስ የሚያካትት ሲሆን በመሰረታዊነት የቡና ማሳን ከኬሚካል፣ ከአረምና ከተባይ መጠበቅ፣ የበሰለ ቡናን ብቻ በመሰብሰብ በአግባቡ ማድረቅ፣ ማከማቸትና ማጓጓዝን የሚያካትት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር ለኢዜአ እንደተናገሩት ባለፈው ዓመት 298 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 1 ነጥብ 43 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል።

ዘንድሮም መጠኑን ወደ 400 ሺህ ቶን በማሳደግ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማግኘት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በቀጣይም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የቡና ዋጋ ተለዋዋጭ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ የሚያጋጥማት የምርት መቀነስ ስጋት እንደሌለ ተናግረዋል፤

የአለም ገበያን መሳብ የሚቻለው በጥራት መሆኑን ገልጸው፣ የቡና ምርት ዱካን ወይም የበቀለበትን አካባቢ በመለየት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ የማድረግና ጥራቱን የጠበቀ የቡና ምርት በጊዜው ለገዢዎች የማድረስ ጉዳይ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የገበያ ዋጋን በድርድር መሸጥ የሚቻለው ከደረጃ 1 እስከ 3 ያሉ ቡናዎች ማቅረብ ሲቻል መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም ጥራት ላይ ሰፊ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በብዛት ደረጃ 4 እና 5 ቡናን ለዓለም ገበያ እያቀረበች መሆኑን አቶ ሻፊ ኡመር ጨምረው ገልጸዋል።

የጥራት ደረጃን በማሻሻል ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዘንድሮው አመት በተለየ መልኩ በቡና ምርት ጥራት ማስጠበቅ ላይ ከአመራሩ ጀምሮ እስከ አምራች አርሶ አደሩ ድረስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

የቡና ምርት ጥራትን ማሻሻል በዓለም አቀፍ ገበያ ዋጋ ከመቀበል ወደ ዋጋ መወሰን በመሸጋገር አምራቹን ተጠቃሚ፤ ሀገር ደግሞ ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ለዚህም በዋነኛነት ከኮሜርሻል ወደ ስፔሻሊቲ የቡና ገበያ ለመግባት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በገበያው ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል ከአምራቹ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት የምርት ጥራት ማስጠበቅ ላይ ይበልጥ መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም