ቀጥታ፡

ላይቤሪያ ብሔራዊ የልማት አጀንዳዎቿን ለማሳካት ከኢትዮጵያ ልምድ መውሰድ ትፈልጋለች-አምባሳደር ሉዊስ ሼሪን ባይሊ

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 15/2017(ኢዜአ)፦ላይቤሪያ ብሔራዊ የልማት አጀንዳዎቿን ለማሳካት ከኢትዮጵያ ልምድ መውሰድ እንደምትፈልግ በኢትዮጵያ የሀገሪቱ አምባሳደር ተናገሩ።

በኢትዮጵያ የላይቤሪያ አምባሳደር ሉዊስ ሼሪን ባይሊ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ሁለቱ ሀገራት ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ወዳጅነት አላቸው ብለዋል።

እንደ አምባሳደሯ ገለጻ ዘመናትን ያስቆጠረው የሁለቱ አገራት ግንኙነት በትራንስፖርትና ሌሎች ዘርፎች እየተጠናከረ መጥቷል።

ከኢትዮጵያ ጋር በጤና፣ትምህርት፣ ግብርና እና ሌሎች በርካታ ዘርፎች በትብብር መስራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በግብርና፣ በመሰረተ ልማትና ሌሎች ዘርፎች ትክክለኛ የልማት ፖሊሲዎችን በመተግበር እያስመዘገበች ያለው የምጣኔ ሀብት እድገት ልምድ የሚወሰድበት እንደሆነ አንስተዋል።

የላይቤሪያ መንግስት ትኩረት ያደረገባቸውን ብሔራዊ የልማት አጀንዳዎችን ለማሳካት ከኢትዮጵያ ልምድና ተሞክሮ ለመቅሰም እንደሚፈልግም ጠቁመዋል።

ሁለቱ ሀገራት ለአፍሪካ ጠንካራ አንድነትና ብልፅግና እውን መሆን ጉልህ ሚና እንዳላቸውም አምባሳደሯ ገልጸዋል።

ላይቤሪያ በአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ማዕቀፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድ ልውውጥ ለማሳደግ እየሠራች መሆኗንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ህዳር 21 ቀን 2017 ዓ.ም ዳግም ወደ ላይቤሪያ ዋና ከተማ ሞንሮቪያ በረራ መጀመሩን በማስታወስ የሁለቱን አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ እንደሚያጠናክረው አስረድተዋል።

ይህም የሁለቱን ሀገራት ትብብር በማሳደግ ረገድ አዲስ መንገድ መክፈቱንም ጨምረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም