ሰብዓዊ ርዳታ የሚሹ ወገኖችን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል በቂ ክምችትና የተሟላ ዝግጅት አለ - አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ሰብዓዊ ርዳታ የሚሹ ወገኖችን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል በቂ ክምችትና የተሟላ ዝግጅት አለ - አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 14/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ እርዳታ የሚሹ ወገኖችን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል አሁናዊ በቂ የሰብዓዊ ድጋፍ ክምችትና ዝግጅት መኖሩን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) ገለጹ።
መንግስት በራስ አቅም ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በማስተጓጎል ጥቅም ይገኛል በሚል የሚንቀሳቀሱ አካላት ከድርጊታቸው ሊታረሙ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት መንግስት በተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች የሚከሰቱ አደጋዎችን መቋቋም የሚያስችሉ ሀገራዊ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ለአብነትም የምግብ ዋስትና እና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ሰብዓዊ ድጋፎችን ከማድረግ ባሻገር ተጎጂዎችን በዘላቂነት ማቋቋም የሚያስችሉ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን አንስተዋል።
በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች የሚከሰቱ አደጋ ስጋቶችን ለመቋቋምና ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ለመድረስ ማህበረሰቡ እርስ በርስ የሚተጋገዝበትን ስርዓት ለማጠናከር ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የመጠባበቂያ ክምችት በመፍጠር ሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም በዘላቂነት ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ሀገራዊ አቅም ለመፍጠር ወደ ስራ መገባቱን አንስተዋል።
በዚህም ካሳለፍነው ክረምት ጀምሮ እስከ በ2017/2018 የምርት ዘመን 253 ሺህ ሄክታር መሬት በማረስ 2 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ወይም 20 ሚለዮን ኩንታል ምርት በማምረት መጠባበቂያ ክምችት ለመያዝ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
እስካሁንም 108 ሺህ ሄክታር መሬት መታረሱን ገልፀው፤ ይህም የዕቅዱን 43 ከመቶ ይሸፍናል ነው ያሉት።
ዕቅዱን ዕውን በማድረግ እንደ ሀገር ሙሉ የመጠባበቂያ ክምችት በመያዝ በፌደራልና በክልል ደረጃ ቀዳሚ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
አሁናዊ ሰብዓዊ ድጋፎችን በተመለከተም በሁሉም አካባቢዎች በጥናት ላይ የተመሰረተ የቅድሚያ ቅድሚያ ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን የመለየትና ተደራሽ የማድረግ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳም ከአንድ ወር በፊት በቤተሰብ ደረጃ እንዲሁም አጠቃላይ ተጋላጭነትን የተመለከቱ ሁለት ጥናቶች መካሄዳቸውን ጠቅሰዋል።
በወቅቱ የጎላ ችግር እንዳልነበር አስታውሰው ነገር ግን በአንዳንድ ኪስ ቦታዎች የምግብ ዋስትና ጋር የተያያዙ ክፍተቶች መለየታቸውን ተናግረዋል።
በአካባቢው የነበረው የጸጥታ ችግር ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ እንቅፋት መፍጠሩንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
ነገር ግን ጉዳዩን ከፖለቲካ ጥቅም ጋር በማያያዝ ላልተገባ ዓላማ የሚያውሉ ወገኖች አጀንዳቸው ከሰብዓዊ ድጋፍ ጋር ትስስር የሌለው መሆኑን ተናግረዋል።
መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ በትኩረት እየሰራ መሆኑንና ከሃይማኖት አባቶችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመናበብ ሰብዓዊ ድጋፎች ለሚፈለገው አካል ብቻ እንዲደርሱ መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
መንግስት በራስ አቅም ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በማስተጓጎል ጥቅም ይገኛል በሚል የሚንቀሳቀሱ አካላት ከድርጊታቸው ሊታረሙ ይገባልም ነው ያሉት።
በየደረጃው ያለ የመንግስት መዋቅር ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት ለሰብዓዊ ርዳታ አቅርቦት በቂ ክምችት እና የተሟላ ዝግጅት እንዳለው ገልጸው ከልማት አጋሮች ጋርም በመናበብ እየሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ከምግብ ድጋፍ ወደ አይበገሬነት ግንባታ ለመሸጋገር የተጀመረውን ጥረት ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።