የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሀገር የተጀመሩ ሥራዎች ውጤት እያስገኙ ነው - አቶ ሰለሞን ላሌ - ኢዜአ አማርኛ
የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሀገር የተጀመሩ ሥራዎች ውጤት እያስገኙ ነው - አቶ ሰለሞን ላሌ
ሀዋሳ፤ ታህሳስ 14/2017(ኢዜአ)፡- የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሀገር የተጀመሩ ሥራዎች ውጤት እያስገኙ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሌ ገለፁ።
በእንሰት ተክልና በስራስር ሰብሎች ላይ ያተኮረው 2ኛው ሀገር አቀፍ የዘርና የምግብ አውደ ርዕይ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል።
በመርሀ ግብሩ ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሌ እንደገለጹት መንግስት የምግብና የሥነ-ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ውጤት እያስገኙ ነው።
እንደ እንሰት ያሉ የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸውን ተክሎች በማስፋፋት ፋይዳቸውን ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላትና ከህብረተሰቡ ጋር ተባብሮ መስራት ይገባል ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የአፈር ለምነትን በመጨመር የግብርና ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማሪዮ በኢትዮጵያ ሀገር በቀል የሆኑ የእንሰትና ስራስር ሰብሎች ከምግብነት ባለፈ የተለያየ ጠቀሜታ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
እንሰት፣ የኢትዮጵያ ድንች፣ አንጮቴ፣ ቦዬና ጎደሬ ከሌሎች ሰብሎች እንደሚለዩ ገልጸው፣ እነዚህ የስራስር ሰብሎች ለማህበረሰቡ በችግሩ ጊዜ የሚደርሱ፣ በበሽታ የመጠቃት ዕድላቸው ያነሰ፣ በትንሽ ስፍራ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ፣ ከምግብና መድኃኒትነት ባለፈ ሌላም ጠቀሜታ ያላቸው ናቸው ብለዋል።
የእንሰት ተክልና የስራስር ሰብሎች በቂ ምርምር ያልተደረገባቸው እንዲሁም የግብርና ኤክስቴንሽን የሌላቸው መሆኑንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ እነዚህን ችግሮች በመፍታት እንሰትና የስራስር ሰብሎች ለምግብ ዋስትናና ለኢኮኖሚ ያላቸውን ሚና ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ በበኩላቸው፣ በክልሉ በአሁን ወቅት ከ100 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በእንሰት ተክል መልማቱን ጠቁመዋል።
በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ተክሉን ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።
አርሶ አደር ብርሀኑ ቡናራ በበኩላቸው በማሳቸው እንሰት በስፋት እንደሚያለሙና ከተክሉም ቆጮ፣ ቡላ፣ ቃጫ እና ሌሎች ምርቶችን እያለሙ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የዳውሮ ዞን ሎማ ቦሳ ወረዳ አርሶ አደር ደብሪቱ ደምሴ በበኩላቸው ጎደሬና እንሰትን ከአዝርዕት ሰብሎች ጋር በማፈራረቅና በማቀላቀል እንደሚያለሙ ገልጸዋል።
በአውደ ርዕዩ ላይ በሲዳማ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች ከእንሰትና ስራስር ሰብሎች የሚዘጋጁ ምግቦች ለዕይታ የቀረቡ ሲሆን በእንሰትና ስራስር ልማት ላይ ያተኮረ ውይይትም ተካሂዷል።