የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መድኃኒት መውሰድ ከእምነት ጋር እንደማይጋጭ ምእመኑን በማስተማር የበኩላችንን እንወጣለን - የሀይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መድኃኒት መውሰድ ከእምነት ጋር እንደማይጋጭ ምእመኑን በማስተማር የበኩላችንን እንወጣለን - የሀይማኖት አባቶች
ሚዛን አማን፤ ታኅሣሥ 14/2017(ኢዜአ)፡- የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መድኃኒት መውሰድ ከእምነት ጋር እንደማይጋጭ ለምዕመናን በማስተማር መድሀኒቱን በማቋረጥ የሚከሰት ሞትን ለማስቀረት የበኩላቸውን እንደሚወጡ የሀይማኖት አባቶች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መድኃኒት አጠቃቀም ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በሚዛን አማን ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
በጉባኤው የባሕሪ ለውጥና ተግባቦት ሥራ አስተባባሪ አቶ በድር አደም እንደገለጹት፣ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መድኃኒትን ማቋረጥ የሞት አደጋን ያስከትላል።
ስለሆነም የሃይማኖት ተቋማት ተከታዮቻቸውን የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መድኃኒት መጠቀም ከእምነት ጋር እንደማይጋጭና መድሀኒቱን ሲያቋርጡ ሊከሰት የሚችለውን ሞት እንዲረዱ ማስገንዘብ ይገባል ብለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢና የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሀጂ መሐመድ ጅብሪል ቁርዐን መድኃኒት መውሰድን እንደማይከለክል ገልጸዋል።
እንደ ሃይማኖት ተቋም አስቀድሞ መጠንቀቅ ላይ በትኩረት ትምህርት እንደሚሰጥ ገልጸው፣ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ወገኖች መድኃኒት ቢወስዱ ከእምነቱ ጋር እንደማይጋጭ እያስተማሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ መልዕከ ሳህል ነቢዩ ፀሐይ በበኩላቸው የእምነቱ አስተምህሮ መድሃኒት መውሰድን እንደማይከለክል ለምዕመናኑ እያስተማሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ቫይረሱ በደማቸው የተገኘባቸው ወገኖችም እምነቱ ከሚያዘው ሥርአት ጎን ለጎን የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መድኃኒታቸውን መውሰድ እንደሚገባቸው የመከሩት ደግሞ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጅማ ቦንጋ ሀገረ ስብከት አገልጋይ አባ ጴጥሮስ አበበ ናቸው።
ቤተክርስቲያኗ በጉዳዩ ላይ ለምዕመናን ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ስትሰራ መቆየቷን አስታውሰው፣ የጸረ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መድሀኒት መውሰድ በእምነቱ እንደማይከለክል ተናግረዋል።
ከፈጣሪ በታች የጤና መመሪያን በአግባቡ አውቆ መተግበር ይገባል ያሉት ደግሞ ከኢትዮጵያ ወንጌላውያን ኅብረት ቤተክርስቲያን የመጡት መጋቤ ፍቃዱ ወልዴ ናቸው።
በተለይ ወጣቶች ራሳቸውን ከመጠበቅ ባለፈ ተመርምረው ራሳቸውን ማወቅና ቫይረሱ በደማቸው ከተገኘም መድኃኒቱን በአግባቡ እንዲጠቀሙ አስገንዝበዋል።
በሚዛን አማን ከተማ በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ የተለየዩ የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።