በቴክኒክና ሙያ ተቋማት የተደረገው ሪፎርም ተቋማቱ ሀገራዊ አቅምን የሚያሳድጉ ችግር ፈቺ ምርቶችን እንዲፈጥሩ አስችሏል- ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
በቴክኒክና ሙያ ተቋማት የተደረገው ሪፎርም ተቋማቱ ሀገራዊ አቅምን የሚያሳድጉ ችግር ፈቺ ምርቶችን እንዲፈጥሩ አስችሏል- ሚኒስቴሩ
አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 14/2017(ኢዜአ)፦ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት የተከናወኑ የለውጥ ሥራዎች ተቋማቱ ሀገራዊ አቅምን የሚያሳድጉ ችግር ፈቺ ምርቶችን እንዲፈጥሩ ማስቻሉን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በማዘመን የሚጠበቅባቸውን አገራዊ ኃላፊነት እንዲወጡ የሚያስችሉ 11 ዋና ዋና የለውጥ ሥራዎች ተከናውነዋል።
በዚህም በየመስኩ አገራዊ አቅምን የሚያሳድጉ በርካታ ውጤቶች ተገኝተዋል ብለዋል።
የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ከሥልጠና ጎን ለጎን ተኪ ምርቶችን እንዲያመርቱና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በመፍጠር ገቢ እያመነጩ መሆኑን አንስተዋል።
ለአብነትም ዘመናዊ የንብ ቀፎና የዶሮ ቤቶችን ከማምረት ጀምሮ በርካታ ችግር ፈቺ ሥራዎች ላይ እንደተሰማሩ አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ከውጪ የሚገቡ ትላልቅ ማሽነሪዎችን የማምረት አቅም በመፍጠር የግብርና ምርት መሰብሰቢያ መሳሪያዎች እና የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያዎችን እየፈጠሩ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ካሉበት አካባቢ ጸጋ ጋር የሚጣጣም አዳዲስ የሙያ ሥልጠና በመስጠት ብቁ የሰው ኃይል እያፈሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመምህራንን አቅም የሚገነቡ ሥልጠናዎች ቀጣይነት ባለው መልኩ ተደራሽ እየተደረጉ መሆኑንም እንዲሁ።
ይህም በየአካባቢው ያሉ ሀብቶችን አሟጦ ለመጠቀም የተያዘውን አገራዊ ግብ የሚያሳካ መሆኑን አብራርተዋል።
የተቋማቱን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግም ስድስት ተቋማት የዓለም አቀፍ ደረጃ አሰጣጥ ድርጅት (አይ ኤስ ኦ) ብቃት ማረጋገጫ እንዳገኙ ገልጸው፥ 33 ተቋማት ደግሞ በሂደት ላይ ናቸው ብለዋል።
የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የለውጥ ሥራ ሀገራዊ ሚናቸውን እያጎለበተ መምጣቱንም ተናግረዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከሶስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች በቴክኒክና ሙያ ተቋማት የመደበኛና አጫጭር ሥልጠናዎችን እንደሚወስዱ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።