ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት አስር ቀናት አብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ደረቅ እና ፀሐያማ ሆነው ይቆያሉ

አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 14/2017(ኢዜአ)፦በሚቀጥሉት አስር ቀናት አብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ እንደሚኖራቸው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዮት አስታወቀ።  

የኢንስቲትዮቱ የሚቲዎሮሎጂ ትንበያና የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምክር አገልግሎት ምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሳምነው ተሾመ፤ ለኢዜአ እንደገለጹት በሚቀጥሉት አስር ቀናት በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ይጠናከራል።

የሌሊትና የማለዳው ቅዝቃዜ በተለይ በአገሪቱ በሰሜን ምስራቅ፣ በሰሜን፣ በምስራቅና በደቡብ ደጋማ አካባቢዎች ላይ በሂደት እየቀነሰ እንደሚሄድ ገልጸዋል። 

በአንዳንድ የአገሪቱ ደጋማ አካባቢዎች ላይ የሌሊቱ እና የማለዳው ቅዝቃዜ በአንፃሩ በሂደት እንደሚቀንስ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ ብለዋል።

በሚቀጥሉት አስር ቀናት የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአየር ትንበያ መረጃዎች ያሳሉም ብለዋል።

የደመና ሽፋን በሂደት እየተጠናከረ እንደሚሄድ የገለጹት ሃላፊው፤ ይህም ለአነስተኛ ዝናብ መፈጠር መንስኤ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

በዚህም እስከ 29 ሚሊ ሊትር ዝናብ ሊኖራቸው እንደሚችል የአየር ሁኔታ መረጃዎች ያሳያሉ ሲሉም ጠቁመዋል።

በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የአገሪቱ ክፍሎች አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ይጠበቃል ብለዋል። 

በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች የሚኖረው ደረቅ የአየር ሁኔታ ለመኸር ሰብል ስብሰባ ተግባራት አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም