በተቋሙ እየተተገበረ ያለው የሪፎርም ስራ ውጤት እየታየበት ነው- የሚሲዮን መሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በተቋሙ እየተተገበረ ያለው የሪፎርም ስራ ውጤት እየታየበት ነው- የሚሲዮን መሪዎች
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 14/2017(ኢዜአ)፦በኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ተግባራዊ የተደረገው የሪፎርም ስራ ውጤት እያሳየ ነው ሲሉ በአዉሮፓ፣አሜሪካ፣ ኤዥያና አውስትራሊያ አገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሲዮን መሪዎች ገለጹ።
የሚሲዮን መሪዎች እና የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የስራ ሃላፊዎች በተቋሙ ተግባራዊ በተደረገው የሪፎርም ስራ ላይ የበይነ-መረብ ውይይት አድርገዋል።
በዚህ ወቅትም በተቋሙ በሚሰጡ አገልግሎቶችና በቀጣይ ተግባራዊ በሚደረጉ የቴክኖሎጂ መር አገልግሎቶች ላይ በዋናነትም የኢ-ፓስፖርት ያለበት ደረጃ፣በተቋሙ በነበሩ ክፍተቶች ላይ የተደረጉ የህግ ማዕቀፍችና ህግን ተላልፈው በተገኙ አካላት ላይ በተወሰዱ እርምጃዎች፣ በተቀናጀ የድንበር አስተዳደር ስራ፣ በሰው ሃይል አደረጃጀት፣ በአሰራር ሂደት ላይ ባጋጠሙ ችግሮች እና በተወሰዱ መፍትሄዎች ላይ ያተኮረ ውይይት ተደርጓል።
በውይይቱ የተሳተፉ የሚሲዮን መሪዎች ተቋሙ ተግባራዊ ባደረገው የሪፎርም ስራ የታዩ መሻሻሎችን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም በሚሲዮኖች ላይ የተመደቡ የኢሚግሬሽን ባለሙያዎች በኤምባሲ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ቀልጣፋ እንዲሆኑ አድርገዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ከቪዛ አኳያ ለሚያጋጥመን ችግር በፍጥነት የሚሰጠው ምላሽ የሚያበረታታ ነው ያሉት አምባሳደሮቹ፥ ወደ ኢ-ፓስፖርት ለመሸጋገር የሚደረገው ዝግጅትና አመራሩ እስከአሁን ለሰራቸው ስራዎች እውቅና መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
በውይይቱ ወቅት የሚሲዮኑ መሪዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ያነሱ ሲሆን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ሃላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ውይይቱን የመሩት የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በተቋሙ የሪፎርም ስራ የመጡ ለውጦችን በማንሳት በኤምባሲ የተጠየቁ አገልግሎቶች ያሉበትን ደረጃ ማየት የሚያስችል የጋራ ስርዓት ለማዘጋጀት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ዳይሬክተሯ አክለውም፥ ከሚሲዮን መሪዎች ጋር በቀጣይ ጠንካራ የስራ ግንኙነትት እንደሚኖር ገልጸው፥ የኢ- ፓስፖርት አገልግሎት በቅርብ እንዲጀመር መረጋገጣቸውን ከተቋሙ የተገኘ መረጃ ያለመክታል።