ቀጥታ፡

የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት የወጥነት ችግርን ለመፍታት በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር እየተዘረጋ ነው- ባለስልጣኑ

አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 14/2017(ኢዜአ)፦ የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ችግርን ከመነሻው እስከ መድረሻው ወጥነት ባለው አሰራር ለመተግበር የሚያስችል ቴክኖሎጂ እየተዘረጋ መሆኑን የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ገለፀ።

ከኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር በነዳጅ ስርጭትና አቅርቦት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት በቡታጅራ ከተማ ውይይት እያካሄደ ነው።


 

የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰሃረላ አብዱላሂ በዚህ ወቅት እንዳሉት መንግስት በድጎማ ለህዝብ ነዳጅ ሌሎችንም በማቅረብ ማህበረሰቡ በኑሮ ጫና እንዳይጎዳ እየሰራ ነው።

የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ችግር ከመነሻው እስከ መድረሻው ባለው የአሰራር ውስብስብነት የሚፈጠር በመሆኑ በቴክኖሎጂ ወጥነት በሆነ አሰራር ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በመንግስት ድጎማ የሚመጣው ነዳጅ በተገቢው መንገድና በፍትሃዊነት ተደራሽ ስለመሆናቸው ጠንካራ ክትትል እንደሚደረግም ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።


 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው በበኩላቸው፤ በነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየትና በመግባባት ለመፍታት አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።

የኑሮ ውድነቱ ለመቆጣጠር የሕገ ወጥ ነጋዴዎችና የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም ደግሞ የማደያ ባለቤቶችን ጨምሮ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር እንደሚሻ ተናገረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም