የአንካራው ስምምነት በአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት እንዲኖር ጎልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል - ኢዜአ አማርኛ
የአንካራው ስምምነት በአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት እንዲኖር ጎልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል
አዲስ አበባ፤ ታህሣሥ 14/2017(ኢዜአ)፦ የአንካራው ስምምነት በአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት እንዲኖር ጎልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ኢዜአ ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያ ገለጹ።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር በር እንዲኖራት ጠንካራ የዲፕሎማሲዊ ሥራ የተሰራበትም ነው ብለዋል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሕግ ባለሙያና አማካሪው አቶ አበበ ጉታ እንዳሉት የአንካራው ስምምነት የአፍሪካ ቀንድ ሠላምና መረጋጋት እንዲሁም ደህንነት እንዲረጋገጥ ትልቅ ዕገዛ አለው።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በቀጣናው ያለው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊና ማህበራዊ መስተጋብርና ትስስር የበለጠ እንዲጠናከር የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያና ሶማሊያ በብዙ ነገሮች የተሳሰሩ በመሆናቸው ስምምነቱ ሁለቱንም ሀገራት ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በዓለም አቀፍ ሕግ የተደገፈና ሕጋዊ መሆኑንም ገልጸዋል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት የዲፕሎማሲ ተቀባይነት የበለጠ እንዲጨምር አድርጓል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የተከተለችው የሰጥቶ መቀበል ዲፕሎማሲያዊ መርህ የቀጣናው ሀገራትን ትስስርና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የአንካራው ስምምነት ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር በር እንዲኖራት ጠንካራ የዲፕሎማሲዊ ሥራ የተሰራበት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የምትከተለው ጎረቤቶቿን መሰረት ያደረገ አብሮ የመልማት እና የጋራ ሰላምና መረጋጋት የማስፈን ተግባር ቀጣናዊ ትብብር እንዲጠናከር ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን የሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም እንዲረጋገጥ በአንድነት መቆም እንዳለባቸው በማሳሰብ አሁን ላይ የባህር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅሟ ነውም ብለዋል።