የቡናን ምርታማነት ለማሳደግ በተሰሩ የሪፎርም ሥራዎች የቡና የወጪ ንግድ ገቢ ጨምሯል - ባለሥልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
የቡናን ምርታማነት ለማሳደግ በተሰሩ የሪፎርም ሥራዎች የቡና የወጪ ንግድ ገቢ ጨምሯል - ባለሥልጣኑ
ሀዋሳ፤ ታህሳስ 14/2017 (ኢዜአ):-የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወኑ ባሉ የሪፎርም ሥራዎች የቡና የወጪ ንግድ በመጠንና በገቢ በፍጥነት እያደገ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ገለፀ።
የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ለቡና ተክል ልማት ውጤታማነት ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ባለስልጣኑ አስታውቋል።
ዘንድሮ ወደ ውጭ የሚላከው የቡና መጠን ከአምናው በ100 ሺህ ቶን ብልጫ እንዲኖረው እየተሰራ መሆኑም ተመክቷል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የግብይት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሻፊ ዑመር ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ በተለይ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በዘርፉ እየተከናወኑ ባሉ የሪፎርም ሥራዎች የቡና የወጪ ንግድ በመጠንና በገቢ በፍጥነት እያደገ ይገኛል።
ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልከው የቡና መጠን በ20 ዓመት ውስጥ ዕድገት የሚያሳየው በ75 ሺህ ቶን ብቻ እንደነበር አስታውሰው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መጠኑን በ100 ሺህ ቶን ለማደግ የፈጀበት ጊዜ አራት ዓመት ሆኗል ብለዋል።
ባለፈው ዓመት 298 ሺህ ቶን ቡና ወደውጭ በመላክ 1 ነጥብ 43 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን አስታውሰው፣ ዘንድሮ መጠኑን ወደ 400 ሺህ ቶን በማሳደግ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማግኘት ታቅዷል ብለዋል።
በግማሽ በጀት ዓመት 200 ሺህ ቶን በላይ ቡና በመላክ 1 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት እንችላለን ነው ያሉት።
የገዢዎችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ጥራት ያለው ቡና በጊዜ ለገበያ በማቅረብ የቡናን የወጪ ንግድበመጠንና በገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደጉን ገልፀዋል።
ባለፉት አምስት ወራት 117 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ ለመላክ ታቅዶ ከ178 ሺህ ቶን በላይ ማሳካት እንደተቻለ ገልፀው፣ ከዚህም 797 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደተገኘ ተናግረዋል።
ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመጠን የ72 በመቶ፤ በገቢ ደግሞ የ55 በመቶ ብልጫ ያለው ነው ብለዋል።
በመንግስት ደረጃ ለቡና የተሰጠው ትኩረት፣ በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ የሪፎርም ሥራዎች ከፍተኛ አስተዋጾ ማበርከቱንም ጠቅሰዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ለቡና ተክል ልማት ውጤታማነት ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ነው የገለጹት።
ቡናን በስፋት በመትከል፣ ያረጁ ቡናዎችን በመጎንደልና የተራዘመ የግብይት ሰንሰለት በማሳጠር ቡናን በብዛትና በጥራት አምርቶ ወደውጭ የመላክ ጥረትም ተጠናክሮ ሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።