ሀገራዊ ምክክሩ ለህዝብ በሚጠቅም ጉዳይ ላይ መወያየትና መመካከር ስለሚያስችል ሰላም ያመጣል - ሰኚ ነጋሳ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ለህዝብ በሚጠቅም ጉዳይ ላይ መወያየትና መመካከር ስለሚያስችል ሰላም ያመጣል - ሰኚ ነጋሳ
አዳማ፤ ታህሳስ 13/2017(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ ለህዝብ በሚጠቅም ጉዳይ ላይ መወያየትና መመካከር ስለሚያስችል ሰላም እንደሚያመጣ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ከፍተኛ አመራር ሰኚ ነጋሳ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የባለድርሻ አካላት አጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ እያካሄደ ነው።
በቅርቡ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋር የሰላም ስምምነት የተፈራረመው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ከፍተኛ አመራር አባላት በአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረኩ ላይ እየተሳተፉ ነው።
በዚሁ ወቅት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ከፍተኛ አመራር ሰኚ ነጋሳ እንደገለጹት፤ በማንኛውም ሁኔታ ግጭት ውስጥ ከመግባት ይልቅ ለህዝብ በሚጠቅም ጉዳይ ላይ በአዳርሽ መወያያትና መመካከር ጠቃሚ ነው።
ይህ ሲሆን ለህዝቡ የሚጠቅም፣ ህዝቡን የሚያቀራርብ ሃሳብ መያዝ እንደሚቻል ገልጸው፤ ምክክሩ ሀገራዊ እንደመሆኑ በህዝቡ መካከል ሰላም ያመጣል የሚል እምነት አለኝ ብለዋል።
ባለድርሻ አካላት ልዩነቶቻቸውን አንድ ላይ በማምጣት ውይይት ከተደረገ ለህዝብ የሚጠቅም ነገር ይዞ መውጣት እንደሚቻልም ነው የተናገሩት።
በምክክሩ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት አንድ ላይ ማወያያት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እንደሚያግዝ አመልክተዋል።