በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማቱ አካል የሆኑት የስፖርት መሰረተ ልማቶች በርካታ ጠቀሜታዎችን እያስገኙ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 13/2017(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማቱ አካል የሆኑት የስፖርት መሰረተ ልማቶች የብስኪሌት ስፖርትን ለማሳደግ አስተዋጿቸው ከፍተኛ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ብስክሌት ፌዴሬሽን ገለጸ፡፡

ፌደሬሽኑ ዛሬን ጨምሮ ለአራት ሳምንታት የሚቆየውን አመታዊ የኮካኮላ የብስክሌት ሻምፒዮና አስጀምሯል፡፡

የብስክሌት ውድድሩ ከሜክሲኮ ሳር ቤት በሚዘልቀውና የኮሪደር ልማቱ አካል በሆነው መንገድ ተካሂዷል፡፡


 

የፌዴሬሽኑ የበላይ ጠባቂ አቶ ረዘነ በየነ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በመዲናዋ የተሰሩት መሰረተ ልማቶች የብስክሌት ስፖርት በህብረተሰቡ ዘንድ ተዘውታሪና ባህል እንዲሆን አስተዋጿቸው የጎላ ነው፡፡

የውድድሩ ዋና አላማ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት እና በኮሪደር ልማቱ የተሰሩ የብስክሌት መንገዶችን ማስተዋወቅ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡


 

የፌዴሬሽኑ የጽህፈት ቤት ሃላፊ ሲሳይ ተረፈ በበኩላቸው፤ በውድድሩ ክለቦች፣ ታዳጊዎች፣ ወጣቶች እና የቀድሞ ብስክሌተኞች እንደተሳተፉበት ገልጸዋል፡፡

ውድድሩ በተለይም በመዲናዋ የብስክሌት ስፖርት በስፋት እንዲዘወተርና ተሰጥኦ ያላቸውን ተተኪ ስፖርተኞች ማፍራት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡


 

ተወዳዳሪዎቹ በበኩላቸው፤ የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ የተሰሩ የብስክሌት ቦታዎች ደህንነታችንን በጠበቀ መልኩ በቂ ልምምድ በማድረግ ውጤታማ እንድንሆን ያስችለናል ብለዋል፡፡

ለብስክሌት ስፖርት ውድድር አመቺ ቦታዎች መሰራታቸው ስፖርቱን ለማሳደግና ተተኪ ተወዳዳሪዎችን ለማፍራት እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም