የኢትዮጵያ የባህር በር መሻት ከሀገራዊ ጥቅም ባለፈ በሰጥቶ መቀበል ቀጣናዊ ትስስርን መርህ ያደረገ ነው - አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር መሻት ከሀገራዊ ጥቅም ባለፈ በሰጥቶ መቀበል ቀጣናዊ ትስስርን መርህ ያደረገ ነው - አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 13/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህር በር መሻት ከሀገራዊ ጥቅም ባለፈ በሰጥቶ መቀበል ቀጣናዊ ትስስርን መርህ ያደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ገለጹ።
አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ለኢትዮጵያ የባህር በር የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እየሰፋ እና እያደገ መምጣቱን የገለጹት አምባሳደሩ፤ ይህን ኢኮኖሚ ማንቀሳቀስ የሚያስችል የባህር በር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት አስተማማኝ የባህር በር የምታገኝበትን ስትራቴጂካዊ አካሄድ እየተከተለች እንደምትገኝም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ተጠቃሚነት የሀገሪቱን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ከማሳለጥ ባሻገር ቀጣናውንና አለም አቀፍ ማህበረሰቡን በልማት ለማስተሳሰር ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑን ተነግረዋል።
ኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን ፍላጎቷን ማስተናገድ የሚያስችል አስተማማኝ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የባህር በር ተጠቃሚነቷን ማረጋገጥ የምትፈልገው ፍጹም ሠላማዊ የሆነ አካሄድን በመከተል ብቻ መሆኑን አምባሳደሩ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ደህንነትና የቀጣናውን ሰላማዊነት አጥብቃ የምትፈልገው ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ለዚህም ኢትዮጵያ በቀጣናው ሽብርተኝነትን ለመዋጋትና ለመከላከል እየወሰደች ያለው ቁርጠኝነት ትልቅ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የባህር በር ጥያቄ በኢትዮጵያ የውጪ ፖሊሲ ውስጥ በጉልህና በድፍረት የማይነሳ ጉዳይ እንደነበር ያስታወሱት አምባሳደሩ፤ ባለፉት ጥቂት አመታት ጉዳዩ በይፋ መነሳት መጀመሩ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት ነው ብለዋል፡፡
የኢትየጵያ ልማትና ብልጽግና ጎረቤት ሀገራትን ጭምር በኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚያስተሳስር ትልቅ የገበያ እድል መሆኑን ነው የገለጹት፡፡