ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የቻን የማጣሪያ ጨዋታዋን ከሱዳን ጋር ታደርጋለች 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 13/2017 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሀገራት ሻምፒዮና (ቻን) የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ዛሬ ከሱዳን ጋር ታካሂዳለች።

የሁለቱ አገራት ጨዋታ ከቀኑ 11 ሰዓት በሊቢያ ቤንጋዚ በሚገኘው ማርታየረስ ኦፍ ፌብሩዋሪ ስታዲየም ይካሄዳል።

ስምንተኛው የቻን ውድድር ከጥር 24 እስከ የካቲት 21 ቀን 2017 ዓ.ም በኬንያ፣ ታንዛንያ እና ዩጋንዳ ጣምራ አዘጋጅነት ይካሄዳል።

በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ኢትዮጵያ የመጨረሻ ዙር ማጣሪያዋን ከሱዳን ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታዋን ታደርጋለች።
ዋልያዎቹ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ዛሬ ያከናውናሉ።

በጊዜያዊ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለጨዋታዎች ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ አድርጎ ቡድኑ ከታህሳስ 3 ቀን 2017 ዓ.ም አንስቶ ልምምዱን በአዲስ አበባ ሲያደርግ ቆይቷል።

ቡድኑ ወሳኝ የማጣሪያ ጨዋታዎቹን ለማድረግ ከትናንት በስቲያ ወደ ሊቢያ ማምራቱ ይታወቃል።

የመጨረሻ ልምምዱንም ጨዋታው በሚከናወንበት ማርታየረስ ኦድ ፌብሩዋሪ ስታዲየም ትናንት ማምሻውን ማድረጉን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

በ64 ዓመቱ ጋናዊ ጀምስ ክዌሲ አፒያ የሚሰለጥነው የሱዳን ብሔራዊ ቡድን 23 ተጫዋቾችን በመያዝ ልምምዱን ሲያደርግ ቆይቷል።

ሁለቱ አገራት የመልስ ጨዋታቸውን ታህሳስ 16 ቀን 2017 ዓ.ም በማርታየረስ ኦፍ ፌብሩዋሪ ስታዲየም የሚያደርጉ ይሆናል።

ኢትዮጵያ በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈች ለውድድሩ ማለፏን ታረጋግጣለች። ከዚህ ቀደም በውድድሩ የሶስት ጊዜ ተሳትፎ አድርጋለች።

በቻን ውድድር አዘጋጆቹን ጨምሮ 19 አገራት ይሳተፋሉ።

በቻን ውድድር ላይ ለመሳተፍ አገራት የማጣሪያ ጨዋታቸውን ከጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም ጀምሮ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። የማጣሪያ ውድድሩ እስከ ታህሳስ ወር መጨረሻ ድረስ ይቆያል።

የአፍሪካ አገራት ዋንጫ (ቻን) የአገር ውስጥ ሊግ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት ውድድር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም