የኢትዮጵያ መጪው ጊዜ የብልጽግናና የሰላም እንደሚሆን ፈረንሳይ እምነቷ ነው-ፕሬዝዳንት ማክሮን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መጪው ጊዜ የብልጽግናና የሰላም እንደሚሆን ፈረንሳይ እምነቷ ነው-ፕሬዝዳንት ማክሮን
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 13/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መጪው ጊዜ የብልጽግናና የሰላም እንደሚሆን ፈረንሳይ እምነቷ ነው ሲሉ ፕሬዝዳንት ኢማኑዌል ማክሮን ገለጹ።
ፕሬዝዳንት ኢማኑዌል ማክሮን፥ኢትዮጵያ ለሰው ልጅ መገኛነት የመጀመሪያ አሻራ ያኖረች ሃገር መሆኗንም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው(ኤክስ) ላይ አስፍረዋል።
በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀው የተመለሱት የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት፥በሁለቱ ሃገሮች መካከል ያለው ግንኙነት በታሪክ ሂደትና በትላልቅ የጋራ ፕሮጀክቶች ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከአምስት አመት በፊት የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ወቅት፥ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር በመሆን የባህልና የቅርስ ጥበቃን ከሳይንሳዊ ፕሮግራም አስተሳስሮ ለመስራት መወሰናቸውን ጠቅሰዋል።
በዚህም መሰረት የፈረንሳይ መንግስት በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የሰራው በዓለም ላይ ልዩ የሆነ የቅርስ ጥበቃ ፕሮጀክት በሚቀጥሉት ወራት ውስጥ ፍጻሜውን የሚያገኝ ይሆናል ብለዋል።
የብሔራዊ ቤተ መንግሥት እድሳት ፕሮጀክትንም በመስራት ዛሬ ላይ የሚያኮራ እውነታ ሆኖ እየታየ መሆኑን ጠቁመዋል።
ወደፊትም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ማሻሻያ እንደሚገድፉ ገልጸው፥በትግራይ ክልል የሰላምና መረጋጋት መሰረት የሆነውን የፕሪቶሪያ ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ትብብር እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።