ፈረንሣይ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች - ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን - ኢዜአ አማርኛ
ፈረንሣይ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች - ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 12/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው የልማት ፕሮጀክቶች ፈረንሣይ ድጋፍ እንደምታደርግ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ገለጹ።
ኢትዮጵያ ያነሳችው የባህር በር ጥያቄ ትክክለኛና የሚደገፍ መሆኑን ፕሬዝዳንት ማክሮን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ፕሬዝዳንት ማክሮን በፈረንሣይ ድጋፍ በኢትዮጵያ የሚከናወኑ ዓበይት የልማት ሥራዎች በጋራ ገምግመዋል።
እድሳት የተደረገለት ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት አሁን የደረሰበትን ውብ ገፅታ እንዲላበስ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት ፕሬዝዳንት ማክሮን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ምስጋና ተችሯቸዋል።
በተጨማሪም ፕሬዝዳንት ማክሮን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናትን ለማደስ የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት የእድሳት ሥራው ግማሽ ያህሉ የተጠናቀቀ ሲሆን ቀሪው ሥራ በቀጣይ ጊዜያት እንደሚጠናቀቅ አመልክተዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በቅርቡ ያካሄደችው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ፈረንሣይና ቻይና ተባባሪ ሊቀ-መናብርት ሆነው በሚመሩት የፓሪስ ክለብ ፕሬዝዳንት ማክሮን ላቅ ያለ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የፈረንሣይ መንግሥት በቀጥታ ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋምና በአውሮፓ ኅብረት በኩል የሚያደርገው ድጋፍ አይተኬ በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ወደፊትም ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ፈረንሣይ በኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ኢንቨስተር በመሆን ሌሎች የአውሮፓ ሀገራትንም አስተባብራ በወሳኝ የኢንቨስትመንት አካባቢዎች በጋራ ለመስራት ሁለቱም መሪዎች መግባባት ላይ ደርሰዋል።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ፕሬዝዳንት ማክሮን ኢትዮጵያ በሠላማዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት እያደረገች ስላለው ጥረት በዝርዝር መክረውበታል።
ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊዮን በላይ ህዝብና ኢኮኖሚዋ በፍጥነት እያደገ ያለች ሀገር እንደመሆኗ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት ሁለቱ መሪዎች የተነጋገሩ ሲሆን በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ለምታደርገው ሕጋዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ፕሬዝዳንት ማክሮን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
በዚህ በኩል ኢትዮጵያ ከፕሬዝዳንት ማክሮን የሚጨበጥ ውጤት ትጠብቃለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረዋል።
ሁለቱ መሪዎች በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ጉዳዮች ዙሪያም በመምከር በጋራ ለመስራትም መግባባት ላይ ደርሰዋል።
ኢትዮጵያና ፈረንሣይ ለ127 ዓመት የዘለቀው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ለትውልድ እንዲሻገር ሀገራቱ አበክረው እንደሚሰሩ መግባባት ላይ ደርሰዋል።
የፈረንሣይና ኢትዮጵያ ትብብር በዓለም ላይ ለየት ያለ ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ማክሮን የላሊበላ አብያተክርስትያናት እና የብሔራዊ ቤተ-መንግሥት እድሳት ማከናወን መቻሉን ትልቅ ኩራት ተሰምቶኛል ብለዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በምጣኔ ኃብታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መነጋገራቸውን በመጥቀስ በተለይ የፈረንሣይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኔትዎርክ መስክ እንደሚሰማሩ ጠቁመዋል።
ለዚህ ደግሞ ከአውሮፓ ባንኮች የ80 ሚሊዮን ዩሮ ገንዘብ የሚቀርብ ይሆናል ብለዋል።
ፈረንሣይ በጤና እና በግብርና መስክ ለኢትዮጵያ ድጋፏን አጠናክራ እንደመትቀጥልም ፕሬዚደንቱ አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ያነሳቸው የባህር በር ጥያቄ ትክክለኛና የሚደገፍ መሆኑን ፕሬዝዳንት ማክሮን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተስፋ የሚጣልባት ሀገር ናት ያሉት ፕሬዝዳንቱ የባህር በር ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ ፈረንሣይ የበኩሏን ሚና እንደምትጫወት አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያና ሶማልያ በቱርኪዬ የደረሱት የአንካራ ስምምነትንም የሚደነቅ ነው ብለውታል።
ፕሬዝዳንት ማክሮን በኢትዮጵያ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ማምሻውን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል።