የስራና ክህሎት ሚኒስቴር የስራ ገበያ የመረጃ ሲስተሞችን ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የስራና ክህሎት ሚኒስቴር የስራ ገበያ የመረጃ ሲስተሞችን ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 12/2017(ኢዜአ)፦የስራና ክህሎት ሚኒስቴር "አይዲያ ኤንድ ስኪል ባንክ" እና "ናሽናል ጆፕ ፖርታል" የተሰኙ ሁለት ተጨማሪ የስራ ገበያ የመረጃ ሲስተሞችን ይፋ አደረገ፡፡
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፤ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የስራ ገበያ የመረጃ ስርዓት (E-LMIS) ስር 23 ማይክሮ የስራ ገበያ የመረጃ ሲስተሞች ሲተገበሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
ዛሬ ይፋ የተደረጉት "አይዲያ ኤንድ ስኪል ባንክ" እና "ናሽናል ጆፕ ፖርታል" የስራ ገበያ የመረጃ ሲስተሞች ደግሞ ወደ 25 ከፍ የሚያደርጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ሚኒስቴሩ የአገልግሎት አሰጣጡን እያዘመነና ለስራ ፈላጊዎች ይበልጥ ምቹና ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልጸው ዛሬ ይፋ የተደረጉት ተጨማሪ አቅሞች መሆናቸውን ተናግረዋል።
"አይዲያ ኤንድ ስኪል ባንክ" (Idea and skill bank) የተባለው መተግበሪያ ሀገር በቀል እና ዓለም አቀፍ የስራ ፈጠራ ሃሳቦች እንዲሁም ምክሮች የሚገኝበት የሃሳብ ባንክ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
በመሆኑም ስራ ፈላጊዎች ባሉበት ቦታ ሆነው ከዚሁ የመረጃ ቋት ለስራ ፈጠራ የሚሆኑ ሃሳቦችን ማግኘት የሚችሉ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ሌላኛው ናሽናል ጆብ ፖርታል ደግሞ (National job portal) የሀገር ውስጥና የውጭ አገር የስራ እድል ለማግኘት የሚያገለግል መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህም ዜጎች ባሉበት ቦታ ሆነው ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ስራ የሚፈልጉበትና የሚቀጠሩበት እድል የሚያገኙበት መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚሁ መተግበሪያ በመጠቀም የሚገኙ የስራ እድሎች ምን አልባትም ከሀገር ሳይወጡ ባሉበት ሆነው መስራት የሚያስችሉ ይሆናሉም ነው ያሉት።