ለቆላማ አካባቢዎች የተሰጠው ትኩረት የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል አቅም የሚፈጥር ነው-ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
ለቆላማ አካባቢዎች የተሰጠው ትኩረት የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል አቅም የሚፈጥር ነው-ቢሮው
ሚዛን አማን፣ ታኅሣሥ 12/2017 (ኢዜአ):- መንግሥት ለቆላማ አካባቢዎች ልማት የሰጠው ትኩረት የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል የሚያስችል አቅምን የሚፈጥር መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በክልሉ በሚገኙ አምስት ቆላማ ወረዳዎች የአየር ሁኔታ መረጃ የመሰብሰቢያ ጣቢያ ለማቋቋም ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር በሚዛን አማን ከተማ አካሄዷል።
በቢሮው የአርብቶ አደር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ጀረጀ በቀለ እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም ቆላማ አካባቢዎችን ለማልማት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ሳይፈጠር ቆይቷል።
መንግሥት ለጉዳዩ በሰጠው ትኩረት የልማት ፖሊሲዎችን ቀርጾ እየተገበረ ሲሆን ይህም የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት ውጤታማ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የቆላማ አካባቢዎችን መልክዓ ምድር ታሳቢ ያደረገ የአየር ንብረት መረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያ ለማቋቋም የተጀመረውን ሂደትም የተሰጠው ትኩረት አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
የመረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያ ለማቋቋም የተመረጡት የመኤኒት ሻሻ፣ መኤኒት ጎልዲያ፣ ማጂ፣ ሱሪ እና ጎባ ወረዳዎች ለእንሥሳት እርባታና ለእርሻ ሥራ ባላቸው ምቹ ሁኔታና እምቅ ሃብት መሆኑን አስተባባሪው ጠቁመዋል።
በእነዚህ አካባቢዎች የአየር ሁኔታ መረጃ ባለመኖሩ ድንገተኛ ከባድ ዝናብን የሚያስከትለው ጎርፍ እና የመሬት ናዳ ችግሮች የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩን ሕይወት እየፈተኑት መሆናቸውን ተናግረዋል።
መንግሥት ይህን ታሳቢ በማድረግ የሚቲዎሮሎጂ መረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያ እንዲቋቋም መወሰኑ ኅብረተሰቡ የተፈጥሮ ክስተቶችን መቋቋም የሚችልበትን አቅም የሚፈጥር ነው።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ፤ አምስቱም የመረጃ መሰብሰቢያ ጣቢዎች ግንባታ በቅርቡ እንደሚጀመርና በተያዘው ዓመት ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል።
አካባቢው ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ወደ ኢኮኖሚ ቀይሮ የኅብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት በተቀናጀ መልኩ ማጠናከር እንደሚገባም ገልጸዋል።
የሚቋቋሙት አምስቱ የመረጃ ጣቢያዎች በራስ አቅም በየ15 ደቂቃ የተሻሻለ መረጃ ወደ ዋናው የመረጃ ቋት በመላክ ለኅብረተሰቡ ተዓማኒ መረጃን ለማድረስ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።