የኢትዮ-ቻይና የፊልምና ቴሌቪዥን ፌስቲቫል መካሔድ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-ቻይና የፊልምና ቴሌቪዥን ፌስቲቫል መካሔድ ጀመረ
አዲስ አበባ፤ ታህሣሥ 12/2017(ኢዜአ)፦ የመጀመሪያው የኢትዮ-ቻይና የፊልምና ቴሌቪዥን ፌስቲቫል በአዲስ አበባ መካሔድ ጀመረ።
ፌስቲቫሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵ የቻይና ኤምባሲ እና ጎፍ ኢንተርቴይመንት በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን ከታኅሣስ 12 እስከ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ መኮንን አዳራሽ በተጀመረው ፌስቲቫል በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ፊልም ‘ሂሩት አባቷ ማነው’ እንዲሁም ሌሎች የኢትዮጵያ እና የቻይና ፊልሞች ለዕይታ ይቀርባሉ ተብሏል፡፡
የፊልም ፌስቲቫሉ መዘጋጀቱ በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል የቱሪዝም፣ የባህል እና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጠናከር እንደሚረዳ ተገልጿል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማህዲ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያና ቻይና በምጣኔ ሃብት፣ በዲፕሎማሲ፣ በፖለቲካ እና በባህል ዘርፎች ታሪካዊና ጠንካራ ግንኙነት አላቸው።
ፌስቲቫሉ በሁለቱ ሀገራት መካከል የባህል ዲፕሎማሲን ለማጠናከር እንደሚረዳም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቸን ሃይ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ቻይና በኪነ-ጥበብ ቀደምት ስልጣኔ ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ፌስቲቫሉ የሁለቱ ሀገራትን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር የባህል ትውውቅን ለማሳደግ እንደሚረዳ ተናግረዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ፤ ፌስቲቫሉ የሁለቱን ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት እና የኢትዮጵያን ባህልና ታሪክ ለተቀረው ዓለም ለማስተዋወቅ ያግዛል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ደግሞ ፊልም የተለያዩ ሀገራትን ህዝብ ባህልና ታሪክ ለማስተዋወቅ እንደሚያግዝ አንስተዋል።
የፊልምና ቴሌቪዥን ፌስቲቫሉ የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና የቆየ ወዳጅነት ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው በኪነ-ጥበብ ዘርፍ ሙያተኞችን ከማፍራት ባለፈ የህዝብ ለህዝብ፣ የባህል እና የታሪክ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ ዓለም አቀፍ ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የጎፍ ኢንተርቴይመንት መስራች አቶ ዑስማን አወል ፌስቲቫሉ የፊልም ገበያውን ለማሳደግ፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ልምድ ለመለዋወጥ ታስቦ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።