ተልዕኳቸውን በብቃት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን የጎንደር ከተማ ሰልጣኝ ሠላም አስከባሪዎች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
ተልዕኳቸውን በብቃት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን የጎንደር ከተማ ሰልጣኝ ሠላም አስከባሪዎች ተናገሩ
ጎንደር ፤ ታኅሳስ 12/2017 (ኢዜአ) ፡- የሠላምና የህግ ማስከበር ተልዕኳቸውን በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የጎንደር ከተማ ሰልጣኝ የሠላም አስከባሪ አባላት ገለጹ።
በወታደራዊ ሳይንስ ግዳጅ አፈፃጸም የንድፈ ሀሳብና የተግባር ሥልጠና የወሰዱ የጎንደር ከተማ ሠላም አስከባሪ አባላት ዛሬ ተመርቀዋል።
አስተያያተቻውን ከሰጡ ሠልጣኞች መካከል አቶ ሰለሺ አስማረ እንዳሉት፤ የሕግ ማስከበር ተልዕኳቸውን በላቀ ብቃት በመፈጸም ለከተማዋ ዘላቂ ሠላም መስፈን እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
ጽንፈኛው ቡድን ከህዝብ ጥቅም በተፃራሪ የቆመ በመሆኑ ይህን ኃይል በቆራጥነት ለመታገል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በከተማው የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ሠላምን ማረጋገጥ ይገባል ያሉት ደግሞ ሰልጣኝ ገበያው ተፈሪ ናቸው።
በከተማዋ ሠላምን በዘላቂነት ለማስከበርና ወንጀልን ለመከላከል የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።
ሠልጣኝ ያየሽ ደሳለኝ በበኩላቸው፤ በተሰጣቸው ሥልጠና ለህዝቡ ሠላም መጠበቅ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በጎንደር ከተማ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈጸሙ የእገታና የጥቃት ወንጀሎችን ለመካለከልና አጥፊዎቹ ህግ ፊት እንዲቀርቡ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ሚሊሻ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አግዬ ታደሰ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ሰልጣኞቹ የህይወት መስዋትነት ጭምር በመክፈል ወንጀሎችን ለመከላከል ተዘጋጅተዋል።
ሥልጠናው የሠላም አስከባሪ አባላትን ግዳጅ የመፈጸም ብቃትን በማጎልበት የአመለካከትና የተግባር አንድነቱን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያግዛቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል ተወካይ ሻለቃ ፈለቀ ሥዩም፤ የሠላም አስከባሪ አባላት የግዳጅ አፈፃፀም ለማሳደግ ሥልጠና በመስጠት ማዕከሉ እየደገፈ መሆኑን ተናግረዋል።
ሥልጠናውን በብቃት ተከታትለው ላጠናቀቁ የሠላም አስከባሪ አባላት የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።