ቀጥታ፡

የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለሰዎች ፍቅር፣ ሰላምና አብሮነት መጠናከር አበክሮ ይሰራል- ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ  

ድሬዳዋ፤  ታህሳስ 12/2017(ኢዜአ) ፡- የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሰዎች መካከል ፍቅርና ሰላምን በመስበክ  አብሮነትን ለማጎልበት ሲያደርግ የቆየውን ድጋፍ  አጠናክሮ እንደሚቀጥል የጉባኤው ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ አስታወቁ። 

 "ሃይማኖቶች ለሰላም፣ ለአንድነት፣  ለአብሮነትና  ለአገር ግንባታ ያላቸው ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ  የሰላም ኮንፈረንስ በድሬዳዋ ተካሄዷል። 


 

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንዳሉት፤ ጉባኤው ለአገር ዘላቂ ሰላም፣ለህዝብ አብሮነትና ፍቅር ማበብ በትጋት እየሰራ ይገኛል።

አገር አቀፍ የሰላም ጉባኤ ድሬዳዋ ላይ ማካሄድ ያስፈለገበት ምክንያትም በጋራ የሚከናወኑ የሰላም ማስከበር ስራዎችና ውጤቶች ልምድ ለመቅሰም በማሰብ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በሰላም አብሮ ከመኖርና ከመከባበር አኳያ በጉባኤው የተከናወኑ አበረታች ተግባራትን ለማጎልበት ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ሼህ ኢብራሂም ኢማም በበኩላቸው እንዳመለከቱት፤ ለአንድ አገር ሁለንተናዊ ጉዞ ማማርና መመንደግ ሰላም ትልቁ ሃብት ነው።

ሰላምን  በዘላቂነት ለመጠበቅ የሁሉም ኃላፊነትና ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል። 

ጉባኤው ሰላምን በማፅናት  የተሻለች አገርና ትውልድ ለማነፅ የሚያደርጉትን ስራዎች በመደገፍ  የድርሻውን መወጣቱን እንደሚቀጥል  ገልጸዋል። 

 የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ድሬዳዋ ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች  በፍቅር፣ በአንድነትና በሰላም ተከባብረው የሚኖሩባት የሰላም ከተማ ናት።  

የአከባቢው ሰላም ተከብሮ የቆየውም  ሁሉም ነዋሪዎች እና አመራር አባላት ተጋግዘውና  ተዋህደው በቅንጅት በመስራታቸው እንደሆነ አውስተዋል።

ሰላምን ይበልጥ ለማፅናት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤  የሰላም ጉባኤው ለማስቀጠል ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም