የሕልመኛ ታዳጊዎችን ተስፋ ያለመለመው ብርሃን የዐይነ ስውራን ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት - ኢዜአ አማርኛ
የሕልመኛ ታዳጊዎችን ተስፋ ያለመለመው ብርሃን የዐይነ ስውራን ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት
አዲስ አበባ፤ ታህሣሥ 12/2017(ኢዜአ)፦ የቀዳማዊት እመቤት ፅሕፈት ቤት ካስገነባቸው ትምህርት ተቋማት መካከል አንዱ ነው- ብርሃን የዐይነ ስውራን ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት።
ትምህርት ቤቱ በአካል ጉዳት ሳቢያ ዕድል ለተነፈጋቸው በርካታ ታዳጊዎች ህልማቸውን ዕውን ያደርጉ ዘንድ ተስፋቸውን አለምልሟል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ተመርቆ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር የተላለፈው አዳሪ ትምህርት ቤቱ፤ ከተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች የተውጣጡ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ተቀብሎ አገልግሎት እየሰጠ ነው።
አዳሪ ትምህርት ቤቱ የተማሪዎቹን የትምህርት፣ የቤተ መፃሕፍት፣ የምግብ እና ሌሎች አገልግሎቶችን ምቹ በሆነ አግባብ እንዲሰጥ ተደርጎ ተደራጅቷል።
ይህ ደግሞ ዐይነ ስውራን ተማሪዎች የትምህርት ዕድል ከማግኘታቸው ባሻገር ምቹና የተሟላ የመማር ማስተማር ስርዓት በመፍጠር ህልማቸውን ብቻ እንዲያስቡ መልካም አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው ተማሪዎችም ትምህርት ቤቱ፤ ሕልማቸውን እንዲኖሩ ተስፋ አሰንቋቸዋል።
የ12ኛ ክፍል ተማሪዋ ያምሮት ካሳሁን፤ በጉልበት ስራ እየሰራች ትማር ከነበረበት ደብረታቦር ከተማ ነው የመጣችው።
ያምሮት እንደምትለው፤ በብርሀን የዐይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት መግባቷ የመማር አምሮቷን እንድታጣጥም ዕድል ፈጥሮላታል።
የ11ኛ ክፍል ተማሪው ሽብሩ አየለ ከሃዋሳ የመጣ ሲሆን ሌላው የክፍል ባልደረባው ቢንያም ጌታቸው ደግሞ ከአርሲ ነው ትምህርት ቤቱን የተቀላቀለው።
የትም አካባቢ ቢሆን ትምህርት ለመከታተል ለዐይነ ስውራን ከባድ ውጣ ውረድ ማለፍ እንደሚጠይቅ ገልፀው፤ ብርሀን የዐይነ ስውራን ትምህርት ቤት ግን ይህን ስጋት አስወግዶላቸዋል።
መንግስት ለዐይነ ስውራን የሰጠው ትኩረት በማድነቅ፤ ትምህርት ቤቱ ሕልመኛ ታዳጊዎች ሽልማቸውን ዕውን እንዲያደርጉ ተስፋ ያለመለመ ተቋም እንደሆነ አስረድተዋል።
የብርሃን የዐይነ ስውራን ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አለም ከበደ በበኩላቸው፤ ትምህርት ቤቱ 312 ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ነው።
ተማሪዎቹ ወደ አዳሪ ትምህርት ቤቱ ከመምጣታቸው በፊት የብሬል ዕውቀት ስልጠና ተሰጥቷቸዋል።
ትምህርት ቤቱ ዕምቅ ችሎታና አቅማቸውን ተጠቅመው ለሀገር የሚተርፍ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ዕድል የሚፈጥር ነው ይላሉ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዐይነ ስውራን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አበራ ረታ በበኩላቸው፤ መንግስት ከለውጡ ጊዜ ጀምሮ አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
የዐይን ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤቶች ባለመኖራቸው ቅሬታ እንደነበራቸው በማውሳት፤ ቀዳማዊት እመቤት ፅሕፈት ቤት ደረጃውን የጠበቀ አዳሪ ትምህርት በማስገንባቱ ትልቅ ውለታ እንደሆነ ይናገራሉ።
ዐይነ ስውራን ወገኖችን ተጠቃሚ ለማድረግ መሰል ጥረቶችን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል።