ቀጥታ፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የመድኃኒት እና ሕክምና መገልገያ አምራቾችን ጥያቄ የፈታ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 12/2017(ኢዜአ)፦የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያው የመድኃኒት እና የሕክምና መገልገያ አምራቾችን የዓመታት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠ መሆኑን የኢትዮጵያ መድኃኒት እና የሕክምና መገልገያ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማህበር ገለጸ፡፡

የመንግሥት ገቢን በማሳደግ ወጪንና የድጎማ ሥርዓትን ውጤታማ ማድረግ፣ በጡረታ ፈንድ ሥርዓቶች ላይ መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን መተግበር፤ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ውጤታማና ተወዳዳሪ ማድረግ እና የብድር አስተዳደርን ማዘመንና ዘላቂ ለማድረግ ከሀምሌ 2016 ዓ.ም ጀምሮ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ገቢራዊ መደረጉ ይታወቃል፡፡

በዚህም ለዓመታት በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሲቸገሩ የነበሩ የወጭና ገቢ ንግድ ድርጅቶች በቂ ምላሽ አግኝተዋል፡፡


 

ከዚህም ባለፈ የአምራች ኢንዱስትሪውን የመለዋወጫ እቃዎች ችግር በመፍታት በሙሉ አቅማቸው ወደ ምርት እንዲገቡ የሚያስችል ሥነ ምህዳር ተፈጥሯል፡፡

ለአብነት የአምራች ኢንዱስትሪው ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኋላ ባለፉት ሶስት ወራት 816 ሚሊየን ዶላር ተኪ ምርቶችን ማምረት የቻለበትን አቅም ፈጥሯል፡፡

የኢትዮጵያ መድኃኒት እና የሕክምና መገልገያ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳንኤል ዋቅቶሌ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በፖሊሲ ማነቆ ምክንያት ሀብቷን ጥቅም ላይ ሳታውል ዘመናትን ተሻግራለች፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ገቢራዊ ከተደረገ በኋላ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ይነሳ የነበረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሙሉ በሙሉ ተፈትቷል ብለዋል፡፡

በተለይም የመድኃኒት እና የሕክምና መገልገያ አምራች ኢንዱስትሪዎች መንግሥት በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ የለያቸውን 123 የመድኃኒት አይነቶች ለማምረት መልካም አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት በሚማቅቁበት ዘመን በዘመናዊ መንገድ መድኃኒት ታመርት እንደነበር አስታውሰው፤ በፖሊሲ ችግር ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ቀድመው መሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከሪፎርሙ በፊት የነበራቸውን 8 በመቶ ድርሻ አሁን ወደ 36 በመቶ ማሳደጋቸውን ገልጸዋል፡፡

መድኃኒት ለሀገር ውስጥ ፍላጎት ከማቅረብ ባለፈ ለውጭ ገበያ በተለይም ለአፍሪካ በማቅረብ ኢትዮጵያ የመድኃኒት ማዕከል ማድረግ የሚያስችል አቅም አለን ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የመድኃኒት እና የሕክምና መገልገያዎችን ለማምረት የተመቸ የአየር ንብረት፣ ፍላጎት፣ እንደ አየር መንገድ ያለ የማጓጓዣ ትራንስፖርት ያላት መሆኗን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መንግሥት ከውጭ ከሚያስገባቸው 262 የመድኃኒት አይነቶች 123ቱ በሀገር ውሰጥ እንዲመረቱ ትልቅ እገዛ ማድረጉን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤  መድኃኒት እና የሕክምና መገልገያዎች የሀገር ህልውና እና የሉዓላዊነት ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም መንግሥት የፈጠረውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የመድኃኒት እና የሕክምና መገልገያዎችን በሀገር ውስጥ ለማምረት ሁሉም መተባበር እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም