ኮርፖሬሽኑ በትግራይ ክልል ውቅሮ ማራይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያስገነባቸውን ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች አስረከበ - ኢዜአ አማርኛ
ኮርፖሬሽኑ በትግራይ ክልል ውቅሮ ማራይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያስገነባቸውን ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች አስረከበ
አክሱም፤ ታኅሣሥ 12/2017 (ኢዜአ)- የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን በትግራይ ክልል ውቅሮ ማራይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባቸውን ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ አስረክበ።
ኮርፖሬሽኑ ከሚያገኘው ገቢ በሰባት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባቸውን አራት ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን ነው ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ያስረከበው።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም በርክክቡ ስነ ስርዓት ላይ እንዳሉት፤ ኮርፖሬሽኑ በዕውቀት የዳበረ ተተኪ ዜጋን ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።
ኮርፖሬሽኑ በየዓመቱ ከሚያገኘው ገቢ ለማህበረሰቡ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ የሚጠበቅበትን ማህበራዊ ሃላፊነት እየተወጣ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከ300 ሺህ ብር በላይ ወጪ የተገዙ ሁለት ሺህ ደብተሮችን ኮርፕሬሽኑ ለተማሪዎቹ በድጋፍ ማበርከቱንም ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ጉዕሽ ኪሮስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ የሰፈነውን ሰላም ተከትሎ በትምህርት ቤቶች ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች እየተስፋፉ ይገኛሉ።
በክልሉ በ2017 የትምህርት ዘመን ከአንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ለትምህርት ቅድሚያ ሰጥቶ ላስገነባቸው ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችም ምስጋና አቅርበዋል።