ኢዜአ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ የሚያከናውናቸውን ሥራዎች ይበልጥ ለማስፋት እየተገበረ ያለው የሪፎርም ሥራ የሚበረታታ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ የሚያከናውናቸውን ሥራዎች ይበልጥ ለማስፋት እየተገበረ ያለው የሪፎርም ሥራ የሚበረታታ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 12/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ የሚያከናውናቸውን ሥራዎቹን ይበልጥ ለማስፋት እየተገበረ ያለው የሪፎርም ሥራ የሚበረታታ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቴ አለነ ገለጹ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የሪፎርም ሥራዎች አፈፃፀም ላይ ያተኮረ ውይይት በአዳማ አካሂዷል።
በውይይት መድረኩ ላይም የኢዜአ የሪፎርም ስራዎችን በተመለከተ ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ገለጻ ተደርጓል።
በተጨማሪም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ እውነቴ አለነ እና ምክትል ሰብሳቢው አቶ አዝመራው አንደሞ የዴሞክራሲ ተቋማት ሊኖራቸው ስለሚገባ ግንኙነት እና ሚዲያና ዲፕሎማሲን የተመለከቱ የውይይት መነሻ ሀሳቦች አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ እውነቴ አለነ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ዴሞክራሲያዊ ስርአት እንዲጎለብት ለማድረግ የዴሞክራሲ ተቋማት ጉልህ ሚና አላቸው።
ትልልቅ ሀገራዊ ህልሞችና ውጥኖች እውን እንዲሆኑ ደግሞ ተቋማቱ ተቀራርበውና ተደጋግፈው መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።
በዚህ ረገድ ኢዜአ አሰባሳቢ ትርክት እንዲገነባና ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር በጎ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
ለብሔራዊ ጥቅምና ለዜጎች መብቶች መከበር እንዲሁም ለመልካም አስተዳደር መረጋገጥ በግንባር ቀደምትነት መሰለፍ እንደሚገባውም ነው የተናገሩት።
ኢዜአ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር የሚያከናውናቸውን ሥራዎች ይበልጥ ለማስፋት እያካሄደ ያለው የሪፎርም ሥራ የሚበረታታ መሆኑንም ገልጸዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ አዝመራው አንደሞ በበኩላቸው፤ መገናኛ ብዙኃን የክህሎት፣ የግንዛቤና የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት አገራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።
ኢዜአ የመንግሥት ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲሁም የገዥ ትርክት ግንባታ ውጤታማ እንዲሆን እየሰራቸው ያሉት ሥራዎች ይበልጥ ማጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈ በዲፕሎማሲ ጉዳዮችም የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅሞች የሚያስጠብቁ የይዘት ስራዎችን የበለጠ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
የኢዜአ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ፤ ኢዜአ አገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ተቋሙ ተልዕኮውን በብቃት እንዲወጣ የሚያስችሉ የማሻሻያ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አብራርተዋል።
ጎን ለጎንም ምቹ የሥራ ከባቢ የመፍጠር ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።
ቋሚ ኮሚቴው ኢዜአ የሚያከናውናቸው አጠቃላይ የሪፎርም ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ተከታታይነት ያለው ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ኢዜአ በአገር ውስጥም በውጭም ተደራሽነቱን ለማስፋት የሚያከናውነው ስራ የሚበረታታ መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣይም ብሄራዊ መግባባት የመፍጠርና የሀገር ገጽታ የመገንባት ተልእኮው እንዲሳካ የበለጠ መትጋት እንደሚገባ አመላክተዋል።