አርብቶ አደር አካባቢዎችን ተደራሽ የሚያደርጉ የሚቲዎሮሎጂ የመረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች እየተስፋፉ ነው- ኢንስቲትዩቱ - ኢዜአ አማርኛ
አርብቶ አደር አካባቢዎችን ተደራሽ የሚያደርጉ የሚቲዎሮሎጂ የመረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች እየተስፋፉ ነው- ኢንስቲትዩቱ
ሚዛን አማን፤ ታኅሣሥ 12/2017(ኢዜአ):- አርብቶ አደር አካባቢዎችን ተደራሽ ያደረጉ የዘመኑ ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸው የሚቲዎሮሎጂ መረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች እየተስፋፉ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ ከመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አርብቶ አደር አካባቢዎች የመረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያ ማቋቋም ላይ ያተኮረ ምክክር እያደረገ ነው።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ እንዳሉት ኢንስቲትዩቱ የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎችን ሰብስቦ በመተንተን በሕይወትና ንብረት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል የሚያስችል ምክረ ሀሳብ ለተቋማት የማቅረብ ሥራ እየሠራ ነው።
ይህን ተግባር በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በአርብቶ አደር አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም የመረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎችን ለማስፋፋት እየተሠራ ነው ብለዋል።
አሁን አገልግሎት እየሰጡ ካሉ 1 ሺህ 372 የመረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች በተጨማሪ በዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ በ15 ደቂቃ ውስጥ በራሱ መረጃ አደራጅቶ የሚሰጥ ጣቢያ ማስፋፋት ላይ ትኩረት መደረጉን ጠቁመዋል።
ከማስፋፊያዎቹ መካከል ከመስኖና ቆላማ ሚኒስቴር ጋር በመተባባር በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አምስት የአርብቶ አደር ወረዳዎች ላይ የሚቋቋመው አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቅርቡ ጣቢያው ሲቋቋም የአካባቢውን አቀማመጥ ታሳቢ ያደረገ መረጃ ሰብስቦ አሉታዊና አዎንታዊ ሁኔታዎችን በመጠቆም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሠራል ብለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ታምሩ ቦኒ በዘርፉ የነበረውን የተደራሽነት ችግር ለመቅረፍ ኢንስቲትዩቱ ላሳየው ቁርጠኝነት አመስግነዋል።
የአየር ንብረት መለዋወጥ የወቅቱ አሳሳቢ ጉዳይ በመሆኑ የመረጃ መሰብሰቢያ ማዕከላት የሚሰጡት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምክረ ሀሳብ ለአካባቢው ትልቅ ትርጉም እንዳለውም ጠቁመዋል።
ሚዛን አማን እየተካሄደ ባለው የመረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያ ማቋቋሚያ የምክክር መድረክ ላይ የፌዴራል፣ የክልሉና የሚመለከታቸው የዞን እንዲሁም የወረዳ ባለ ድርሻ አካላት ተገኝተዋል።