ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ለምክክሩ ግብአት የሚሆን አሻጋሪ ሃሳብ ማመንጨት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ለምክክሩ ግብአት የሚሆን አሻጋሪ ሃሳብ ማመንጨት አለባቸው
አዳማ፤ ታህሳስ 12/2017(ኢዜአ)፡- ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ለአገራዊ ምክክሩ ግብአት የሚሆን አሻጋሪ ሃሳብ በማመንጨት የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው ተመለከተ።
" ተመካክረን ኢትዮጵያን እንገንባ፤ እኔም ለሀገሬ እመክራለሁ" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ባዘጋጀው መድረክ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ እና ታዋቂ ግለሰቦች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ወይዘሮ ሂሩት ገብረስላሴ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳድሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተከናውኗል።
በኦሮሚያ ክልል ከታህሳስ 7/2017ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ በቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ ከ7ሺህ በላይ የማህበረሰብ ተወካዮች መሳተፋቸውን አወስተዋል።
አጀንዳ የማሰባሰቡ ሂደትም ነፃና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መከናወኑን አስረድተዋል።
የክልሉን ማህበረሰብ ወክለው በአገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ 320 ተወካዮች መመረጣቸውንም አስታውቀዋል።
ዛሬ ከፖለቲከኞች ፣ ከታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ጋር እየተካሄደ ያለው መድረክ ለአገራዊ ምክክሩ ግብአት የሚሆን ሀሳብ ለማሰባሰብ መሆኑን ገልጸዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች አገርን የሚያሻግር ሀሳብ በማመንጨት የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት አለባቸው ብለዋል።
ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ አገርን ለማሻገር የሃሳብ መሪዎችና በጎ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ሚና የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ ለቀጣይ ትውልድ ጭምር የምትመች አገር በምክክር ለመገንባትና ችግሮቻችንን በዘላቂነት ለመፍታት አሻጋሪ የሆነ ሃሳብ በማመንጨት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል።