ቀጥታ፡

የማንሰራራት ዘመን አብነት የሆነው የማዕድን ዘርፍ እመርታ

ኢትዮጵያ ተፈጥሮ ሁሉን አድሏታል። መሬቷ የሰጡትን አብቃይ ነው። አብቃይ ብቻ ሳይሆን ገፀ ምድሯና ከርሰ ምድሯም በማዕድን የበለጸገ ነው። ውሃ ሀብቷ የቀጣናው ‘ውሃ ማማ’ ያሰኛታል። የብዝዝሃሕይወቷ፣ የአየር ንብረቷና በእንስሳት ሀብቷም  ‘ሁሉ በደጄ’ ያሰኛታል። በዓለም ላይ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጧም ስትራቴጂካዊ ስፍራ ያደርግታል። የሕዝብ ብዛቷም ሌላው ዕምቅ አቅም ነው። ይህ ሁሉ ተፈጥሯዊ ዕምቅ ጸጋዋ ወደ ብልጽግና ማማ ከፍታ ይወስዳታል።

ጸጋዋን በቅጡ ለይታ ከተጠቀመች ከራሷ አልፎ ለሌሎችም ትተርፋለች። የዜጎቿን ማህበራዊ ፍላጎቶችንም ትመልሳለች። ባለፉት ዓመታት ያልታየ ጸጋዋን በማየት ሁሉን አቀፍ የሆነ መዋቅራዊ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ለማረጋገጥ ሁሉን አቀፍ ጥረት ተጀምሯል።

እስካሁን እምብዛም ትኩረት ያላገኙ ዘርፎች ተለይተው ወደ ልማት ተገብቷል። በዚህም የማንሰራራት ዘመን ማሳያ የሆኑ ተጨማሪ ዘርፎች አሉ። ከነዚህም መካከል የማዕድን ዘርፉ ይጠቀሳል። ይህ ጽሁፍ የማዕድን ዘርፉን ለማንሰራራት ዘመን ያለውን አብነታዊ ጉዞ ይቃኛል።

በማዕድን ግብይት አዋጅ 1144/2011 እንደተተረጎመው ማዕድን ማናቸውም ዋጋ ያለው በጠጣር፣ በፈሳሽ ወይም በጋዝ መልክ በተፈጥሮ በመሬት ላይ ወይም ውስጥ፣ በውሃ ውስጥ ወይም ስር የሚገኝ በጂኦሎጂ ሂደት ወይም ሁኔታዎች የተፈጠረ ቁስ ነው።

ማዕድን በአገልግሎቱ፣ በዋጋው እና በሌሎች መስፈርቶች በብዙ መልኩ ይገለጻል። ለምሳሌ የከበረ ማዕድን፣ በከፊል የከበረ ማዕድን፣ ብረት ነክ ማዕድን፣ የኢንዱስትሪ ማዕድን እና የግንባታ ማዕድን ተብሎ።

ኢትዮጵያ ተዝቆ በማያልቅ ማዕድን ከብራለች። ወርቅ፣ አልማዝ፣ የተፈጥሮ ጋዝ፣ ኤመራልድ፣ ብረት፣ መዳብ፣ ኳርተዝ፣ የድንጋይ ከሰል፣ ፓታሽ፣ ጂፕሰም፣ ላይምስቶን፣ እብነ በረድ፣ ባዛልት፣ ሳፈየር፣ ታንታለም፣ አሸዋ እና የሸክላ አፈር… ሌላም ሌላም። ዳሩ ይህ ጸጋ በቅጡ ለይታ እንዳልተጠቀመች ዕሙን ነው::

                  

ከማዕድን ጸጋዎች ትሩፋት የመቋደስ ጅማሮ

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ገቢራዊ መሆን የጀመረው የሀገር በቀል ማክሮ ኢኮኖሚ ረፎርም አምስት ምጣኔ ሀብታዊ ምሰሶዎች ለይቷል። ከነዚህ መካከል አንዱ ማዕድን ነው። በመንግስት የ10 ዓመት መሪ ልማት ዕቅድም የማዕድን ዘርፉ በሚገባ ተቃኝቷል። ለዘርፉ እመርታ አስቻይ የሆኑ ፖሊሲዎችና ሕግ ማዕቀፎች ወጥተዋል። በተለይም የተሻለ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር እና የግል በማዕድን ልማት ዘርፍ ተሳትፎው እንዲያድግ ምቹ ዕድል ተፈጥሯል። የመንግስት መሰረተ ልማት ግንባታ እና ሌሎች ቁልፍ እርምጃዎች ለግሉ ዘርፍ መተማመን ፈጥሯል።

እንደ ሀገር የማዕድን ሀብቶችን በመለየት ለሀገር ልማት ወሳኝ ድርሻ በሚኖራቸው አግባብ እንዲለሙ የሚጠቁሙ ጥናቶች ቀጥለዋል። ተስፋ ሰጭ የጥናት ግኝቶችም አሉ። ለአብነትም ኢትዮጵያ የኮፐር፣ ኒኬል፣ ኮባልት፣ ሊቲየም እንዲሁም ሌሎች ውድ እና ለኃይል አማራጭ የሚውሉ የማዕድን ሀብቶች እንዳሏት በጥናት ተረጋግጧል።

ለኮንስትራክሽን የሚውሉ እንደ ዕነበረድ፣ ግራናይት፣ ላይምስቶን ፣ ባዛልት፣ አሸዋ፣ ጠጠር፣ ኢግኒምብራይትና የሸክላ አፈር፤ ለኢንዱስትሪ የሚውሉ እንደ ካኦሊን፣ቤንቶናይት፣ ኳርትዝ፣ የድንጋይ ከሰል፣ ላይምስቶን፣ ፖታሽ እና ግራፋይት እንዲሁም ለብረታ ብረት ዘርፉ የሚውሉ እንደ ኒኬል፣ ማንጋኒስ፣ ነሃስ እና እርሳስን ጨምሮ ሌሎችም ማዕድናት አሏት።

ጸጋዋን ለማልማት ደግሞ ከማስተዋወቅ ይጀምራል። የማዕድን ሚኒስቴር በዘመኑ ቴክኖሎጂ የታገዘ የማዕድን ጋለሪ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ለጎብኚዎች ክፍት አድርጓል። ለአልሚዎችም ለተመራማሪዎችም ምቹ የግንዛቤ ሁኔታ ይፈጥራል። በየዓመቱም የውጭና የሀገር ውስጥ የዘርፉ ኩባንያዎችን ያሳተፈ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ እየተደረገ ነው። ሕገ ወጥ ግብይትን ለማስቆም የሚያስችል ስራም ተጀምሯል። የማክሮ ኢኮኖሚው የተሟላ ሪፎር ትግበራ ደግሞ ዘርፉን ከማስተዋወቅ ወደ ልማት እንዲገባ ሌላ ዕድል አምጥቷል። ዘርፉን የማስተዋወቅ፣ መረጃዎችን የማደራጀት፣ ምቹ የኢንቨስትመንት ሕግ ማዕቀፍ እና ማበረታቻ ስርዓቶች ተዘርግተዋል።

በ10 ዓመት መሪ ዕቅዱ የማዕድን ዘርፍ በየዓመቱ 33 በመቶ ዕድገት እንዲኖረው ይጠበቃል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ2016 ዓ.ም የማዕድን እና ቴክኖሎጂ(ማይንቴክስ) ኤክስፖ ላይ ለዘርፉ ልማት የተሰጠው ትኩረት ከውጭ ገቢ ማዕድን ግብዓትን መተካት ብቻ ሳይሆን ወደ ውጪ በመላክም የሀገርን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያለመ መሆኑን ገልጸው ነበር። ማዕድን ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና ለምታደርገው ጉዞ መሰረት የሚሆን ወሳኝ ዘርፍ መሆኑንም እንዲሁ።

           

የማዕድን ዘርፍ የእስካሁን እመርታና አበርክቶ

በ10 ዓመት መሪ ዕቅድ ከዘርፍ 17 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ግብ ተቀምጧል። በተለይም የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ኢኮኖሚውን እንዲደግፍ ታልሟል። ማዕድን ሚኒስቴር እ.አ.አ በ2023 ባወጣው መረጃ 170 የአገር ውስጥ እና ውየጭ ኩባንያዎች በወርቅ፣ ነዳጅ፣ ብረት፣ ጂኦ ተርማል እና መሰል የማዕድን ሀብቶች ፍለጋ እና ልማት ላይ ተሰማርተዋል።

በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ስራ ዕድል ፈጥሯል። በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላኩ ማዕድናት 420 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ 800 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ይጠበቃል። በሩብ ዓመቱም ከግማሽ ቢሊዮን ዶላርበላይ  ገቢ ተገኝቷል።

ከማዕዳናት መካከል የወርቅ ማዕድን የውጭ ምንዛሬ አንቀሳቃሽ ሞተር ቢባል ማጋነን አይሆንም። ወርቅ የ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት የማዕድን ዘርፍ ወጪ ንግድ ገቢ 70 ከመቶውን ይሸፍናል። በተያዘው ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራትም 561 ሚሊዮን ዶላሩ አስገኝቷል።

ይህን አቅም ይበልጥ ለማሳደግ ዘመናዊ አመራር መከተል፣ የወርቅ ግብይት ሕጋዊነት እና የምርት ጥራት ማረጋገጥ እና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግ ላይ ተተኩሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በጋምቤላ ክልል የሚገኘውን “ኢትኖ ማይኒንግ” የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካ በቅርቡ መመረቃቸው ይታወቃል። የፋብሪካው መገንባት የወርቅ አንቨስትመንት በአጭር ጊዜ ያሳየውን አመርቂ ውጤትና ደረጃውን የጠበቀ የወርቅ ምርት ከማስገኘቱ ባሻገር ሕገ ወጥ ለሆነ የማዕድን ስራም ምላሽ የሚሰጥ እንደሆነ ገልጸዋል።

በዘንድሮው በጀት ዓመት ከወርቅ ወጪ ንግድ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን በመጠቆምም፤ በቀጣይ ኩባንያው የወርቅ ምርትን በዕጥፍ ለማሳደግ ተጨማሪ አቅም እንደሆነ ጠቅሰዋል።

                           

                                                ቀጣይስ?

መንግስት ከወርቅ ማዕድን በተጨማሪ በኦፓል፣ ድንጋይ ከሰል እና ሌሎች ማዕድናት የወጪ ንግድ ገቢ ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ የብረት ኢንዱስትሪ መንደር የሚገኘውን ስቲሊ አር. ኤም. አይ ኃላ/የተ/የግ/ የብረታ ብረት ማምረቻ ፋብሪካ መጎብኘታቸው ይታወቃል። መንግስት የማዕድን ዘርፍ በማልማት ከዘርፉ ሀገራዊ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ እንደሆነ በወቅቱ ገልጸዋል።

የጎበኙት የብረታ ብረት ፋብሪካም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት የሚኖረውን ቁልፍ ሚና ጠቅሰዋል። መንግስት ለዘርፉ ፈተና የሆኑ እንደ ጸጥታ ችግር፣ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ እና የአሰራር ማነቆዎች ለመፍታት ለዘርፉ እመርታ በትኩረት እንደሚሰራበትም አረጋግጠዋል።

በጥቅሉ የማዕድን ሀብት ልማት ለኢትዮጵያ ማንሰራራት ዘመን አብነት ሆኗል። የእስካሁን ጅማሮ ተስፋ ሰጪነት ቀጣይ የማዕድን ዘርፉ የኢትዮጵያ በረከት እንደሚሆንና  ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም እንደሚሆን እርግጥ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም