ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ኬንያ በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 11/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ኬንያ በተለያዩ የትብብር መስኮች ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጎልበት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር አድርገዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዛሬ በኬንያ የስራ ጉብኝት አድርጓል።

ልዑካን ቡድኑ ኬንያ ባለስልጣናት ጋር ውይይት አድርጓል።

ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከኬንያ የውጭ እና የዲያስፖራ ጉዳዮች ሚኒስትር እና የካቢኔ ተቀዳሚ ዋና ፀሐፊ ሙሳሊያ ሙዳቫዲ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ ኢትዮጵያ እና ኬንያ ያላቸውን ጠንካራ ትብብር ይበልጥ ማጎልበት እና አዳዲስ የትብብር አማራጮችን መለየት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።

በተጨማሪ ልዑካን ቡድኑ ከኬንያ የኢነርጂ እና ነዳጅ ሚኒስቴር የካቢኔ ፀሐፊ ኦፒዮ ዋንዳይ ጋር ሁለቱ አገራት በታዳሽ ኃይል እና በዘላቂ ኢኒርጂ ልማት ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይም መክረዋል።

የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ኢ/ር ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ፣ የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አንዱዓለም ሲዓ (ኢ/ር) እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበን ያካተተ መሆኑን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ እና ኬንያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እ.አ.አ በ1963 መጀመራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም