ቀጥታ፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የአምራች ኢንዱስትሪውን በማሳደግ አካታችና ዘላቂ እድገት ለማረጋገጥ መሰረት እያኖረ ነው - አቶ መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 11/2017(ኢዜአ)፦ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ አካታችና ዘላቂ እድገት ማረጋገጥ የሚያስችል መሰረት እያኖረ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ፡፡

ሀገር በቀል ኢኮኖሚ እና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ትግበራ ለአምራች ኢንዱስትሪው ያመጣው መልካም ዕድል፣ ተግዳሮት እና መፍትሔዎች ላይ ያተኮረ የመንግሥትና የግል ዘርፉ የምክክር መድረክ በአዳማ ተካሂዷል፡፡


 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፤ መንግሥት ባለፉት ዓመታት የማምረቻ ኢንዱስትሪውን በመደገፍ ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት በትኩረት ሰርቷል።

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ እና የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ለአምራች ኢንዱስትሪው አስቻይ የንግድና ኢንቨስትመንት እድል ፈጥረዋል ብለዋል።

በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ የነበረውን ማነቆ ለመፍታት ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የአስር ዓመት መሪ የልማት እቅዱን መነሻ ያደረገ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።


 

በኢትዮጵያ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ቀላል እየሆነ የመምጣበት አውድ ተፈጥሯል ያሉት ሚኒስትሩ

የአምራች ኢንዱስትሪው በፖሊሲ ማነቆ ምክንያት ቀላል የሆኑ ነገሮች ሁሉ ውድና ከባድ ሆነውበት መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተዘግተው የነበሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት እንዲገቡ እና የማምረት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ማስቻሉንም አንስተዋል።

በዚህም ለውጭ ገበያ የተለያዩ ምርቶችን በማቅረብ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት መጀመራቸውን ነው የተናገሩት።

ተኪ ምርቶችን በማምረት የአምራች ኢንዱስትሪውን የሀገር ውስጥ የገበያ ድርሻ ከፍ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ፖሊሲው የኢንዱስትሪ ምርቶችን ገበያ ታሳቢ ያደረጉ እና የማምረቻ ኢንዱስትሪው በግሉ ዘርፍ እንዲመራ የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዚህም የአምራች ኢንዱስትሪው ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኋላ ባለፉት ሶስት ወራት 816 ሚሊየን ዶላር የሚያወጡ ተኪ ምርቶችን ማምረት መቻሉን ገልጸዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት እመቤት መለሰ(ዶ/ር)፤ የባንኩ ምስረታ ብዙ ዓመታትን ቢያስቆጥርም በተለያዩ ምክንያቶች አስቸጋሪ ሁኔታዎች ማለፉን አንስተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የአምራች ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ ከ92 ቢሊየን ብር በላይ ለግሉ ዘርፍ ፈሰስ አድርጓል ብለዋል፡፡

በክልል ለሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸው፤ በብድር የተሰጠው ገንዘብ ሳይመለስ ቀርቶ ለመንግሥት ተጨማሪ እዳ አይሆንም ብለዋል፡፡


 

የጀርመን ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያ ፕሮግራም ሃላፊ አና ዋልዳማን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለኢትዮጵያ አዲስ የእድገት ምዕራፍ ነው ብለዋል፡፡

ድርጅቱ ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ከግሉ አምራች ኢንዱስትሪ ጋር በትብብር ይሰራል፤ አስፈላጊውን ድጋፍም ያደርጋል ነው ያሉት።


 

የኢትዮጵያ መድሀኒትና ህክምና መገልገያ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳንኤል ዋቅቶሌ በበኩላቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግርን መፍታት አስችሏል ብለዋል፡፡

በዚህም በሀገር ውስጥ አምራቾች የሚሸፈነው የመድሀኒት ፍላጎት አሽቆልቁሎ 8 በመቶ ደርሶ እንደነበር ገልጸው፤ ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኋላ ወደ 36 በመቶ ማደጉን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም